ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት የሚመጥን የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር በትኩረት ይሰራል – ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር)

ነሐሴ 16/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት የሚመጥን የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር በትኩረት ይሰራል ሲሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህን የገለጹት በሩሲያ ሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ሮዛ የሩቅነህ ጋር በበይነ መረብ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

ውይይቱ የሩሲያ ባለሃብቶች በአግሮፕሮሰሲንግ፣ በማኑፋክቸሪግ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በአውቶሞቢል እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ በትኩረት እንደሚሰሩ የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

በሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ሮዛ የሩቅነህ በበኩላቸው ሩሲያውያ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ለፍላጎቱ ተግባራዊነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ በቀጣይ በሩሲያ በሚካሄዱ አለምአቀፍ የቢዝነስና የኢንቨስትምንት ፎረሞች በመሳተፍ ፍላጎት ካሳዩ ኢንቨስተሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን በማካሄድ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ የሩሲያ ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተመላክቷል።