ከሕመም የተቀዳ ጥበብ



ሥዕል መሣል የጀመረው ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ በተመለከተው የእህቱ ፎቶግራፍ እንደነበር ይናገራል፡፡ ሠዓሊ ሽፈራው ፍቅሬ በሕመም ምክንያት ቤት እስከዋለበት ጊዜ ድረስ የሥዕል ተሰጥኦ እንደነበረው አያውቅም ነበር፡፡

በሥዕል ሥራዎቹ ከኢትዮጵያ አልፎ በሌሎች የዓለም ሀገራት ኢትዮጵያን የማስጠራት ሕልም ያለው ወጣቱ ሠዓሊ የመጀመርያ የሥዕል ሥራው ከ19 የሥዕል ሥራዎች ጋር ተወዳድሮ አራተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጂዳ ወረዳ የተወለደው ሽፈራው አፈር ፈጭቶ፤ ውሃ ተራጭቶ በሚወደው ቀዬ አደገ።

ይሁን እንጂ ሽፈራው በ14 ዓመቱ ሕመም አጋጠመው። ለሕክምናም አያቱ ወደ አዲስ አበባ አመጡት። ከዚህ በኋላ ከአጋጠመው የታዳጊነት ዘመን ሕመም በመጠኑ ቢያገግምም ፍፁም ጤንነትን አላገኘም፡፡ እግሮቹ ለከፍተኛ ሕመም ተዳረጉ፡፡ ለመቦረቅ ሰፈር የሚጠበው፣ ለመጫወት ድካም ማይገድበው ሽፈራው እንደ ልጅነቱ ለመቦረቅ አልታደለም፡፡ እግሮቹ አልንቀሳቀስ፤ አናንቀሳቅስ አሉት፡፡ ቤት ውስጥ ለመዋል ተገደደ፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀን ከተቀመጠበት ቦታ ሆኖ ዓይኞቹ አሻግሮ ግድግዳ ላይ ከተሰቀለው የእህቱ ፎቶግራፍ ላይ አሳረፋቸው፡፡ ፎቶውን ደጋግሞ ተመለከተ፡፡ እርሳስና ወረቀት አስማምቶ፤ የእህቱን ፎቶ ወደ ሥዕል ለመቀየር አቀረቀረ፡፡

ይህ ጅማሮው ግን እዚህ ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል ግምት እንዳልነበረው ሽፈራው ይናገራል። በተደጋጋሚ በመሞከር እና ለውጡን በማስተዋል ከሰዎች የሚሰጡትንም የማበረታቻ ሀሳቦች ስንቅ በማድረግ አሁን የተዋጣለት ሠዓሊ ሆኗል።

የእህቱን ፎቶ በመሣል አሐዱ ብሎ የጀመረው ሠዓሊነት ከ19 የሥዕል ተወዳዳር አራተኛ በወጣባት የመጀመሪያ ሥዕሉ ተበረታትቶ ቀጠለ፡፡ በሌላ ጊዜ ለጨረታ የቀረበለት ሥዕል 14ሺሕ ብር ተሸጠ። ወጣቱ ሠዓሊ ከዚህ ገንዘብ ላይ የተወሰነ ጨምሮ ስልክ በመግዛት ሥራዎቹን በቲክቶክ እያስተዋወቀ ቀጥሏል።

ጥበብ መንገዷም መገለጫዋም ለየቅል ነው፡፡ በሽፈራው ፍቅሬ በኩል የተገለጠችበት መንገድ አስደናቂ ነው፡፡ ሕመም አሳስሮ ከቤት ያዋለውን ታዳጊ ባጋጠመው ችግር ውስጥ ከጥበብ ጋር ተገናኝቷል።

በእርግጥ ሽፈራው በሥዕል ብቻም ሳይሆን በሌሎች የሥነ-ጥበብ ተሰጥኦዎች ላይ የተካነ ነው፡፡ ቦርሳ፣ ሹራብ እና መሰል የእጅ ስራዎችን ይሰራል።

ሽፈራው በአጋጠመው የእግር ሕመም ምክንያት የአካል ጉዳተኛ ነው፡፡ የአካል ጉዳቱ ግን ከታላቁ ጉዞው አላሰናከለውም፡፡ ከራሱ አልፎ ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችል ብርቱ እና መንፈሰ ጠንካራ ነው።

በአመለወርቅ መኳንንት