ከተሞቻችን-ደባርቅ

ደባርቅ የ340 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ከተማ ናት፡፡ በደጃች አምሳሌ ዘሴ በሚባሉ የአከባቢው ገዢ እንደተቆረቆረች ይነገርላታል፡፡

ከመደናዋ አዲስ አበባ 830 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከባህር ዳር 282 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና የቱሪስት መዳረሻ ከተማ ናት።

ከተማዋ ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 750 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን ሜዳማ እና ተራራማ ተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጥ አላት፡፡ በደጋማ የአየር ፀባይም ትታወቃለች።

ስትመሰረት “ኮሶ መንደር “በመባል ትጠራ የነበረችው ከተማዋ የአሁን መጠሪያዋ ደባርቅ “የእርቅ ስፍራ “የሚል ትርጓሜ እንዳለውም የስነ-ጽሁፍ ምሁራን ያስረዳሉ።

ከንግድ እና ቱሪዝም በተጨማሪ በዙሪያዋ በምታበቅላቸው ሰብሎች እንዲሁም በጋማ እና ቀንድ ከብት እርባታ የምትታወቅም ከተማ ናት፡፡ ከሚመረቱ አዝርዕት መሀከልም ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ እና ምስር ተጠቃሽ ናቸው።

የሊማሊሙ ሸለቆ አፋፍ ላይ ያለችው ደባርቅ ከተማ በዩኔስኮ ለተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፖርክም የመግቢያ በር ነች።ፓርኩ ከከተማዋ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

በከተማዋ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሲሆን በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገነባው ደባርቅ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ ዋሊያ፣ ነባሩ፣ ምቃራ የ1ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም ደባርቅ ዩኒቨርስቲ እና ደባርቅ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያላት ደባርቅ ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ ሆቴሎች እና ሎጆች ባለቤት ስትሆን ሰሜን ሎጅ፣ ራስ ደጀን ሆቴል፣ ሊማሊሙ ሎጅ፣ ጃዝሚን፣ ሶና እና ፀሀይ ዘለቀ ሆቴል ይገኙበታል።

በደባርቅ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁ የኖራችሁባት እና በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትውስታችሁን አጋሩን። መልካም ሳምንት !!

በአዲስዓለም ግደይ