“ከአልጋዬ ፈንቅለው አንስተው ህይወቴን አተረፏት” – ፍቅሬ ስዩም



ፍቅሬ ስዩምን አስታወሳችሁት? የጨርቆሱን፤ እንደውም የሚተኛበት አልጋም ሆነ ፍራሽ በሌለው ትንሽዬ ጎጆ ውስጥ ሆኖ ለዘመናት በህመም ሲሰቃይ የነበረው፤ እንደውም እኔንስ ተዉኝ ልጄን ግን አብሬ ገደልኳት እያለ ከራሱ በላይ ለአብራኩ ክፋይ የሚያለቅሰው፤ እንደውም የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራቱን በውሃ ያሳለፈው ምስኪን ወጣት…. ፍቅሬ ስዩም? አስታወሳችሁት?

አሁን ፍቅሬ ስዩም ላይ የዳመነው ዳመና እየተገፈፈ የመጣ ይመስላል፡፡ በአዲስ ዋልታ ትብብርና በመቄዶንያ ደግነት እነዛ የስቃይ አመታቱ ወደ መልካም ዘመን ተመልሰዋል፡፡ የናፈቀችውን ፀሐይ እየወጣ መሞቅ ጀምሯል፡፡ ልብሱ፣ ንፅህናው፣ ምግቡ እና መድሃኒቶቹ ሰዓታቸውን ጠብቀው ይቀርቡለታል።

የ13 አመቱ ልጅም ጠዋት ጠዋት እየተነሳች እሱን ማስታመም ትታ ወደ ትምህርቷ መሄድ ጀምራለች፡፡ ልጁን የሚያስተምሯት የጨርቆስ ጎረቤቶቹ ናቸው፡፡ “ዋናው ለእሱ እንኳን ደረሳችሁ እንጂ እሷማ ልጃችን ናት እናሳድጋታለን” ሲሉ ነው ቃል የገቡት፡፡

ይህ ሁሉ ተዓምር በሶስት ወር ብቻ የሆነ ነው፡፡ ፍቅሬ ስለ ጉዳዩ ሲያስታውስ የአዲስ ዋልታ ባልደረቦች ድንገት ቤቴ መጥተው ከአልጋዬ ፈንቅለው አንስተው ሕይወቴን አተረፏት በማለት ይጀምራል።

ስለ መቄዶንያ ቆይታውም ሲገልጽ “ሰው ምን ያህል ብር ቢከፈለው በዚህ ደረጃ ለሰው ያዝናል?” ሲል እምባው ይቀድመዋል፡፡ ምንም ሳይጠየፉኝ በየሰዓቱ አፅድተውና ገላዬን አጥበው አዲስ ሰው ያደርጉኛል፡፡ ለእነሱ ቃላት የማይገልፀውን ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ ብሏል፡፡

እንዲሁም በጣም በብዙ የሚናፍቁኝና ዛሬ ለመኖሬ ምክንያት የሆኑ ጓደኞቼ ፣ የጨርቆስ እናቶችና የድድ ማስጫ ወጣቶችም ሁሌም በልቤ ይኖራሉ፤ ሙሉ በሙሉ ድኜ ውለታችሁን የምከፍል እንድሆን ፀሎታችሁ አይለየኝ ሲል ገልጿል፡፡

በእየሩስ ወርቁ