ግንቦት 28/2014 (ዋልታ) በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የመጀመሪያው የወጣቶች ኦሎምፒክ የብስክሌት እና የአትሌቲክስ ዉድድሮች ተጠናቀዋል።
8ኛ ቀኑን ባስቆጠረው 1ኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ የተለያዩ ውድድሮች ፍፃሜያቸውን እያገኙ ሲሆን ዛሬ የብስክሌት እና የአትሌቲክስ ውድድሮች ፍፃሜን አግኝተዋል።
አምስት ክልሎች በተሳተፉበት የብስክሌት ውድድር አዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል።
ዛሬ በ80 ኪሎ ሜትር የወንዶች የጎዳና ላይ ውድድር የተካሄደ ሲሆን ደጋጋ ዘላለም ከአዲስ አበባ 1ኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል።
በውድድሩ እያሱ እሸቱ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የብር ሜዳሊያ ሲያገኝ ተስፋው ተገኝ ደግሞ ከደቡብ ክልል የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነኗል።
በውድድሩ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር በወንድም በሴትም 6 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል።
የመጀመሪያው ወጣቶች ኦሎምፒክ የአትሌቲክስ ውድድር ዛሬ ሲጠናቀቅ የተለያዩ የፍፃሜ ውድድሮች ተደርገዋል።
በአትሌቲክስ ውድድደር አጠቃላይ አዲስ አበባ 20 የወርቅ፣ 12 የብር እና 13 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት 1ኛ ሆኗል።
የኦሮሚያ ክልል በ6 ወርቅ፣ 8 ብር እና 7 ነሐስ በማግኘት 2ኛ ሲሆን የደቡብ ክልል በ4 ወርቅ፣ በ2 ብር እና በ3 ነሐስ 3ኛ ሆኗል።
የሲዳማ ክልል ደግሞ በ2 የወርቅ በ5 የብር እና በ6 ነሐስ ሜዳሊያ 4ኛ በመሆን ውድደሩን አጠናቋል።
መሰረት ተስፋዬ (ከሀዋሳ)