የምግብ ዋስትና ሥራዎች ኢትዮጵያ ራሷን ችላ ለምትቆምበት መፃዒ ተስፋ በር የሚከፍት ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ነሐሴ 27/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ሥራዎች እና የምግብ ሉዓላዊነት መንገድ በጠንካራ ትብብሮች ተሻግሮ ሀገራችን በአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶች ሳትበገር ራሷን ችላ ለምትቆምበት መፃዒ ተስፋ በር የሚከፍት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ በዘላቂ የግብርና ሥራ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የአቅም ግንባታ ሥራ ኢትዮጵያ ምርታማነትን ማላቅ፣ የአዝርዕት አይነትን ማብዛት ብሎም የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ማሻሻል ትችላለች ብለዋል።

እንደዚህ አይነቶቹ ትብብሮች የማኅበረሰብን አቅም ከፍ ያደርጋሉ፣ የኢኮኖሚ ዕድሎችን ይፈጥራሉ እንዲሁም ፈጠራን ያበረታታሉ ሲሉም አክለዋል።

ይህም ኢትዮጵያን በዘላቂ የምግብ ሥርዓት መሪ ያደርጋታል፤ የበለፀገ የምግብ ዋስትና የተረጋገጠበት መፃዒ ጊዜንም ለህዝባችን ያረጋግጣል ነው ያሉት።