የሻምበል ማሞ ወልዴ የኦሊምፒክ ትውስታ

ሻምበል ማሞ ወልዴ ውልደቱ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ አዳአ ወረዳ ነው። ከ1953 እስከ 1955 ባለው ጊዜ ማሞ በኮሪያ በተሰማራው የኢትዮጵያ ቃኘው ሻለቃ የሰላም አስከባሪ ጦር ውስጥ ያገለገለ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ለረዥም ጊዜ የሚታወቅበትን የሩጫ አትሌትነት ህይወቱን ጀመረ ::

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ መድረክ በተሳተፈችበት የ1956ቱ የሜልበርን ኦሎምፒክ ማሞ ወልዴ በ800 እና በ1 ሺህ 500 ሜትር እንዲሁም በ4 በ400 ሜትር የዱላ ቅብብል የሩጫ ውድድር በሶስት ውድድሮች ልምድ ቀስሞ ተመለሰ።

በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከመካከለኛ ወደ ረጅም ርቀት ውድደር በመሸጋገር በ1964 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ በ10 ሺህ ሜትር አራተኛ ደረጃን ይዞ ጨረሰ ።

በ1968ቱ የሜክሲኮ ኦሊምፒክበማራቶን ተወዳዳሪ ሆኖ በተሳተፈበት ወቅት የሁለት ወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው አበበ ቢቂላ በእግር ጉዳት ውድድሩን ከ15 ኪ.ሜ በኋላ ለመቀጠል ሳይችል ቀረ። በውድድሩ ማሞ አደራውን ተቀብሎ በአስደናቂ ሁኔታ ተከታዮቹን በ3 ደቂቃ ልዩነት ጭምር በመቅደም አሸናፊ ሆነ።

በዚህም በተከታታይ 3 የኦሊምፒክ ማራቶን ውድድር የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ እንዲል አድርጓል።

ከማራቶኑ ድል 5 ቀን ቀደም ብሎ ደግሞ በ10 ሺህ ሜትር የተፎካከረው ማሞ፣ ጠንካራ ትንቅንቅ በማድረግ ኬንያዊውን ናፍታሊ ቴሙ ተከትሎ በመግባት ለሀገሩ የብር ሜዳሊያ  አስገኝቷል ::

በ1972ቱ የሙንክ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ39 ዓመቱ ከወንድሙ ደምሴ ወልዴ ጋር ወደ ጀርመን ተጉዞ የነሐስ ሜዳሊያን ማግኘት ችሏል።

በማራቶን የኢትዮጵያን ክብር ከፍ ካደረጉ አትሌቶች መካከል የሚጠቀሰው ይህ ጀግና አትሌት በአጠቃላይ በ4 የኦሊምፒክ ተሳትፎ 3 ሜዳሊያዎችን ለሀገሩ አስመዝግቧል ።

በመጨረሻም በትራክ፣ በሀገር አቋራጭ እና በጎዳና ላይ ውድድሮች ከአፍሪካ እስከ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጲያን የወከለው ሻምበል ማሞ ወልዴ በከባድ የጉበት በሽታ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዬ።

በአክሊሉ ማሬ