የአካዳሚዎቹ ስምምነት ለታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋቾች ምን ተስፋ ይዞ ይመጣል?

የኢዲዋይ አካዳሚ ሰልጣኝ ታዳጊዎች

ኢትዮጵያ በሩጫ ውድድር በተለይም በመካከለኛና በረጅም ርቀት ስሟ በዓለም የገነነ ነው። ወደ እግር ኳስ ስንመጣ ከጅማሬው ደማቅ ታሪክ ቢኖረውም ውጤት እየራቀው ከመጣ ሰነባብቷል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ 1957 የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽንን ከግብፅና ሱዳን ጋር በመሆን ከመሰረቱት አገራት አንዷ ናት። እ.ኤ.አ በ1962 የተካሄደውንና ራሷ ያዘጋጀችውን የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ውድድርም አሸናፊ ነበረች።

በአፍሪካ እግር ኳስ ላይ ታላቅ አሻራ ያሳረፈችው ኢትዮጵያ ግን በአሁኑ ወቅት ምድብ ድልድል ውስጥ ለመግባት እንኳ ስትቸገር ማዬት የተለመደ ሆኗል።

ከመስራች አገሮች አንዷ የሆነችው ግብፅ በአህጉሪቱ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ካላት አስተዋፅኦ አንጻር የተሳካ ታሪክና የእግር ኳስ ዕድገት ላይ ትገኛለች። የአህጉሪቱን ዋንጫ ከየትኛውም አገር በላይ ሰባት ጊዜ በማሸነፍ ደማቅ ታሪከና ጠንካራ የእግር ኳስ ቡድኖችም ገንብታለች።

ለዚህ ደግሞ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወጡት ያዳጊዎች የእግር ኳስ አካዳሚዎቿ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ታላላቆቹ የአውሮፓ የእግር ኳስ ቡድኖች እንደ ባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድ፣ ሊቨርፑለና ፒኤስጂን ጨምሮ በርካታ የታዳጊዎች እግር ኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚዎች በግብጽ ተከፍተዋል።

ኢዲዋይ አካዳሚ ከቲኤፍ ኤ ኢሊት (TFA Elite) ኃላፊዎች በኢዲዋይ አካዳሚ

በርካታ የምዕራብ እና ሰሜን አፍሪካ አገሮች የአውሮፓ ታላላቅ የእግር ኳስ ቡድኖች የታደጊ እግር ኳስ አካዳሚዎች በብዛት የተስፋፉባቸው የአህጉሪቱ አካባቢዎች ናቸው።

ወደኛ አገር ስንመለስ በጣም ጥቂት ከሚባሉና በውስብስብ ችግሮች ከተተበተቡ የእግር ኳስ ቡድኖች የታዳጊዎች ማሰልጠኛ አካዳሚዎች ከመኖራቸው ውጭ ይህ ነው የሚባል የሚታወቅ ዓለም አቀፍ ማሰልጠኛ እንዲኖረን አልታደልንም።

ከቀርብ ጊዜ ወዲህ በግለሰቦች ደረጃ ባለ ተሰጥኦ ወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለማሰልጠን አካዳሚ የከፈቱ ባለሙያዎች መኖራቸው ይታወቃል። ከነዚህ ውስጥ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና የድሞው የብሔራዊ ቡድን እና የቡና እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቹ እድሉ ደረጄ ተጠቃሽ ናቸው።

የቀድሞው ተጫዋችና የአሁኑ አሰልጣኝ እድሉ ደረጄ ኢዲዋይ አካዳሚ (EDY Academy) መስርቶ ታዳጊዎችን በመመልመል ስልጠና መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመት ሆኖታል።

ማሰልጠኛው ከወዲሁ አበረታች ውጤት ማየት የጀመረ ሲሆን በቅርቡ ያሰለጠናቸው ወጣቶች በምድብ አንድ ለኢትዮጵያ ቡናና ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ቡድኖች ተጫዋቾችን እንዲፈርሙ አስችሏል።

በቀጣይም ፕሮፌሽናል ተጫዋች ለማፍራት ከሌሎች አገራት የእግር ኳስ ማሰልጠኛዎች ጋር ስምምነት ፈርሞ ወደ ስራ መግባቱን እድሉ ደረጄ ከአዲስ ዋልታ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።

እድሉ የአገራችን ማሰልጠኛዎች ችግሮችን አስመልክቶ ሲገልጽ በኢትዮጵያ ለታዳጊዎች እግር ኳስ ተጫዋቾች ትኩረት አለመሰጠት፣ የማሰልጠኛ ቦታዎች እጥረት፣ የቁሳቁስ፣ የአሰልጣኞች የአቅም ችግር፣ የአሰራር ስርዓት አለመኖር እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን ያነሳል።

የወጣቶች የእግር ኳስ ልማት ስራን ለማስፋፋት በተግዳሮትነት ካነሰቸው ነጥቦች አንዱ በኢንቨስትመንት ደረጃ መንግስት የሚያመቻቸው መሬት ከስፖርቱ ውጭ ለሆኑ ልማቶች መሆኑ እና ስፖርቱን ለማስፋፋት ከሚያስፈልገው ሰፊ መሬት አንጻር የተሰራ ስራ አለ ለማለት ይቸግራል ይላል አሰልጣኝ እድሉ።

ኢዲዋይ አካዳሚ ከቲኤፍ ኤ ኢሊት (TFA Elite) ከሚባል በዱባይ የሚገኝ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ቡድን ጋር በትብብር ለመስራት ስምምነት አድርገዋል። ቲኤፍኤ በዱባይ ሊግ በሶስተኛ ዲቪዚዮን ይወዳደራል። ትልቅ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣት ተጫዋቾች በዋናው ቡድን ከማስፈረም በተጨማሪ ወጣቶችን እየመለመለና ስልጠናም እየሰጠ ወደ አውሮፓ መላክ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል።

የኢዲዋይ አካዳሚ ወጣቶች በአውሮፓ እግር ኳስ ቱር

የቲኤፍኤ ኢሊት አካዳሚ ቴክኒካል ዳይሬክተር አሊ ኢል ጃኢሽ በስልክ በሰጡን መረጃ ኢትዮጵያ በርካታ የእግር ኳስ ተስጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች መኖራቸውን በመገንዘባችን ነው ከኢዲዋይ አካዳሚ ጋር ለመስራት የተስማማነው ብለዋል። አካዳሚያቸው ምስራቅ አፍሪካን ጨምሮ በመላው ዓለም ላይ ልዩ ችሎታ ያላቸው ታዳጊዎችን የመመልመልና ማሰልጠኛዎች የሚጠይቁትን ደረጃ እንዲያሟሉ የማብቃት ስራ ይሰራል ብለዋል።

ለአብነት ያክል ከዓመት በፊት ሁለቱ ማሰልጠኛዎች ባደረጉት ዓለም አቀፍ የታዳጊዎች ምልመላ ስምምነት መሰረት ናትናኤል አረጋዊ የሚባል ታዳጊ ተጫዋችን በመመልመል ወደ ቲኤፍ ኤ አካዳሚ ገብቶ ከሰለጠነ በኋላ ከአስር ሀገራት ከመጡ ተጫዋቾች አንደኛ በመውጣት ለአካዳሚው መፈረሙን ሁለቱ ኃላፊዎች ገልጸዋል።

ይህንን መነሻ በማድረግ ሌሎች ልዩ ችሎታና ብቃት ያላቸው እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለማፍራት የሁለቱ አካዳሚዎች ግንኙነት መመስረቱን አሰልጣኝ እድሉ ነግሮናል።

ከዛም ባለፈ የቲኤፍኤ ሰዎች ከዱባይ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ፣ ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች በዱባይ ባሉ ዩንቨርስቲዎች ስኮላርሽፕ እንዲያገኙ በማመቻቸት፣ በቲኤፍ ኤ ታች ባሉ ቡድኖች እንዲታቀፉ እና ሌሎች ድጋፎች እንዲያገኙ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጿል። አሰልጣኝ እድሉ አክሎም 18 ዓመት የሞላቸው ታዳጊዎች ኢንተርናሽናል ቡድን እንዲያኙ ጥረት በማድረግ ረገድም ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን ጠቀሷል።

የሁለቱ የታዳጊ እግር ኳስ ማሰልጠኛዎቹ በትብብር መስራት በአገራችን ዘመናዊ የእግር ኳስ አሰለጣጠን ስርዓትን፣ የዕውቀት ሽግግርን፣ አቅም ግንባታና ለታዳጊዎች ዓለም አቀፍ ፕሮፌሽናል በርን ከመክፈት አንጻር የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

 

በቴዎድሮስ ሳህለ