የኢትዮ-ቱርክ ትብብርና የጠላቶች ስጋት

 

በደረሰ አማረ

——————

ዓለም አቀፍ ተንታኞች ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከሯ “ስትራቴጂካዊ” ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የሆነችው ግብጽ ከቱርክ ጋር ያላት ግንኙነት በሻከረበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያና የቱርክ ግንኙነት መጠናከር ብዙ ትርጉም አለው።

የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ተንታኙ አብዱራህማን ሰይድ “ግብጽና ቱርክ ከአንድ በላይ በሆነ ምክንያት ሆድና ጀርባ እየሆኑ መምጣታቸውን ያትታል።

“ግብጽና ቱርክ ቁልፍ በሚባለው የምሥራቅ ሜዲትራንያን የነዳጅ ሃብትን በተመለከተ፣ በሊቢያ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሱዳን ጉዳይ ላይ ተፃራሪ አቋም ነው ያላቸው” ይላል ተንታኙ።

በአንፃሩ “ሱዳንና ግብጽ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር ያላቸው ግንኙነት እየተጠናከረ  ቢመስልም፤ በተቃራኒው ከቱርክ ጋር ክፉኛ የሚቃረን አቋም ነው ያላቸው።

ቱርክ ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ከተመለከትን ደግሞ አዲሱ የሱዳን አስተዳደር እርምጃዎች በአንካራ በኩል ቁርሾ ፈጥረዋል።

ይህ የአንካራ ቁርሾ መነሻ አምባገነኑ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር በስልጣን በነበሩበት ወቅት ቱርክ ከሱዳን ሱዋኪም የተባለችውን ደሴት ተከራይታ ታስተዳድር ነበር። ደሴቷም በቀይ ባሕር ቀጠና ውስጥ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ሚና ትጫወታለች።”

ታዲያ የቱርክ ቅራኔ መነሾ ግዛቲቱን ከቱርክ ለመንጠቅ ወታደራዊው የሽግግር መንግስቱ ግፊት እያሳደረ መገኘቱ ነው።

ይህ ሁኔታ አንካራ በሱዳኑ የሽግግር አስተዳደር ላይ ቂም እንድትቋጥር አደርጓታል። የዚህ ሴራ ጠንሳሿ ደግሞ ግብፅ እንደሆነች አንካራ ታምናለች።

በሌላ መልኩ ደግሞ አሜሪካ በምታራምደው የውጭ ፓሊሲ የተነሳ ቱርክ እና የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም የቱርክ እና የአሜሪካ ግንኙነት እየሻከረ ሄዷል።

በተለይ የፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይብ ኤርዶጋንን መንግሥት ለመገልበጥ በተደረገው ሙከራው ውስጥ  የአሜሪካ መንግሥት  እጅ አለበት ብላ አንካራ መክሰሷ ቅራኔውን አባብሶታል።

እንዲሁም አንካራ ከሞስኮ የጦር መሳሪያ ገዝታለች በሚልም አሜሪካ በ ቱርክ ላይ ተደጋጋሚ ማዕቀብ ስትጥል እንደነበር ይታወቃል።

 

በነዚህ ሁኔታዎች “ቱርክ፤ ከአሜሪካ፤ ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት በጥርጣሬ እንድትመለከተው አስችሏል።

ከዚህ አንጻር በብዙ መልኩ ቱርክ ኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ ከሚገኙ ሀገራት ጋር ስትነጻጸር ተፃራሪ አቋም አላት።

የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ አህመደፍ በቅርቡ ቱርክ ጉብኝት ማድረጋቸው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት አንድ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል፡፡ የኢትዮ-ቱርክ ትብብር አንድ ደረጃ ከፍ ማለቱ እነዚህ ሀይላት በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን አቋም እንደገና እንዲያጤኑ ያስገድዳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ቀንድ ስነምድራዊ ፓለቲካ ተንታኞች ኢትዮጵያ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅማ፤ የጣምራ ጠላቶቿን አቋም አቅጣጫ ማስቀየር ትችላለች ይላሉ።

ከዚህም ከፍ ሲል የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ትብብር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተፅዕኖ ለማስፋት ያስችላታል ሲሉ ፅፈዋል።

ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን አንካራ ጎራ ብለው ከቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶልጉ ጋር ከመወያየታቸው በተጨማሪ በቱርክ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዲስ ህንጻ መመረቃቸው ይታወሳል።

በወቅቱም ካቩሶልጉ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ለምታደርገው ትግል አድናቆት ከመቸራቸውም በላይ አገራቸው በዚህ ዘርፍ እንደምትተባበርም ቃል ገብተው ነበር።

ያኔ ኢትዮጵያና ቱርክ በቅርቡ ምን አይነት ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል? የሚለው ጥያቄ የካይሮና ካርቱም ራስ ምታት ብቻም ሳይሆን የምዕራቡ ዓለም የአፍሪካ ቀንዱ ተዋንያን ትኩረት ሆኖ ቆይቷል።

ከአራት ሳምንታት በፊት የቱርክ ፕሬዚዳንት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ ከተወያዩ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ ቱርክ ለኢትዮጵያ ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ታደርጋለች ማለታቸው  እንቅልፍ የነሳቸው የሱዳኑ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀ መንበር አብዱል ፈታህ አል ቡርሀን ወደ አንካራ ተጉዘው ደጅ ጠንተዋል።

አንዳንዶች የሊቀመንበሩን የአንካራ ጉዞ ጉንጭ አልፋው ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ ሲሉ በሰውዬው ላይ ተዘባብተውበታል።

የቀጣናው የጂኦ ፓለቲካ ተንታኖች እንደሚሉት ከሆነ በአፍሪካ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ግንኙነት በማጠናከር ላይ የምትገኘው ቱርክ ባልተረጋጋው እና ውጥረት በነገሰበት የአፍሪካ ቀንድ የኃይል ሚዛን መፍጠር ትችላለች ብለው ያምናሉ።

አንካራ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ለአፍሪካ ልዩ ትኩረት ሰጥታ መስራት ከጀመረች ከአውሮፓውያኑ 2005 ጀምሮ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ብሄራዊ ጥቅም አለን የሚሉ ሀገራት በሙሉ የቱርክን እንቅስቃሴ በአንክሮ እየተከታተሉ ነው።

ኢትዮጵያ እና ቱርክ 125 ዓመታትን የዘለቀ ታሪካዊ ግንኙነቶች ያላቸው በመሆኑ የስነምድራዊ ፓለቲካ አሰላለፉ በመተማመን ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያስችለዋል ይላል የቱርኩ የዜና ወኪል አናዶሉ።

ለረዥም ጊዜ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በአብዛኛው በኢኮኖሚው ላይ ያተኮረ ነበር።

ከዚህ ባለፈ ግን በአንድም የታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ከቱርክ የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት ተፈራርማ እንደማታውቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉን ጨምሮ ከ200 በላይ የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ ሲሆን ከ30 ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል ፈጥረዋል።   አጠቃላይ ካፒታሉም ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡

ቱርክ ኢኮኖሚያዊ ኢንቨስትመንቶችን ኢትዮጵያ ውስጥ በማከናወን ከቻይና በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ከመሀንዲስ ዶት ኔት የተገኘ መረጃ ያመለክታል። በዚህም ምክንያት ቱርክ ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት አበክራ እንድትሰራ ያስገድዳታል።

በትግራይ ክልል የሚካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቱርክ ኢንቨስትመንቶችን አደጋ ላይ የሚጥል መሆን እንደሌለበት ታምናለች።

ሁለቱ መሪዎች በዋነኝነት አጀንዳ አድርገው የተወያዩት ‘በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል በተከሰተው የድንበር ይገባኛል ውጥረትና የሀገራቱን ወታደራዊ ትብብር በማጠናከር’ ላይ እንደነበር አናዶሉ ዘግቧል።

የሁለትዮሽ ውይይቱ ፍሬ ነገር አዲስ አበባና አንካራ ወታደራዊ የትብብር ስምምነት መፈራረማቸው ይፋ መሆኑ ላይ ነው።

ምንም እንኳን የወታደራዊ ስምምነት ማዕቀፉን በተመለከተ ግልፅ የሆነ ነገር ባይኖርም የኢትዮ-ቱርክ ትብብር ከኢኮኖሚ ወደ ወታደራዊ ትብብር ከፍ ማለቱን መናገር ይቻላል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።

ያሁኑ የኢትዮጵያ አካሄድ ወቅቱን የሚመጥን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ልንለው እንችላለን።

የሁለቱ ወገኖች ትብብር፤ የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ እያሴረ ያለውን ደባ ለመቋቋም እንደሚችል ይታመናል።

ስምምነቱ በራሱ የኢትዮጵያን ተፃራሪ ሀይሎች የሚገዳደር፤ የአፍሪካ ቀንድ አማራጭ አጋር ሀገር መኖሩን ያረጋገጠ ነው፡፡ በሌላ መልኩ የኢትዮጵያ የወቅቱ ጠላቶች ዘንድ ስጋት ይፈጥራል።

በፕሬዘዳንት ኤርዶሃን ግብዣ ወደ ቱርክ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ቱርክ በአስፈላጊ ሰዓት ያሳየችውን ወዳጅነት አደንቃለሁ” ብለዋል።

ቱርክ አከራካሪ በሆነው የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር መግባባት ላይ እንዲደረስ ፍላጎት ማሳየቷ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና እያደገ የመጣውን የግብፅ ተጽዕኖ እና ተፎካካሪነት ለመግታት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል።

ኤርዶጋን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተውን ጦርነት በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “ግጭቱ በሰላም እንዲፈታ ፍላጎት አለኝ፤ ግጭቱን ለመፍታት ሀገሬ የተቻላትን ሁሉ ታደርጋለች” ነበር ያሉት።

 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከአናዶሉ  ጋር በነበራቸው ቆይታ “ቱርክ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ውዝግብ የማስታረቅ ሚና ብትጫወት ኢትዮጵያ ትቀበላለች ማለታቸው ይታወሳል።

የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዙሪያ ከተፈጠረው አለመግባባት ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላት ግንኙነት እንዲያሽቆለቁል ሆኗል።

ኢትዮጵያ በገጠሟት ተግዳሮቶች ምክንያት ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስባለች።

ተንታኞቹ እንደሚሉት ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ጠንካራ አጋሮች ያስፈልጓታል። ከቱርክ ጋር መወዳጀቷ ለጥያቄው ትክክለኛ መልስ ነውም ይላሉ።

አንካራ በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ የጦር ሰፈር ያላት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ቱርክ ከኢትዮጵያ እምብዛም የራቀች ሀገር አይደለችም።

ቱርክ በ ወታደራዊው ዘርፍ በተለይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በማምረት በኩል ጠንካራ አገር ሆናለች፡፡

በቅርቡም በአዘርባጃንና በአርሜኒያ መካከል በተደረገው ግጭት የቱርክ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ መዋላቸው እንዴት የጦርነቱን ውጤት እንደቀየረው ማስተዋል ያሻል። በነዚህ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ጠላቶች አቋም ለዘብተኛ ባህሪ ሊያሳይ እንደሚችል ይታመናል።

ከሰሞኑም የቀጣናውን የሽብር ቡድን ለማዳን ደፋ ቀና ሲሉ ምዕራባውያን የዓቋም ለውጥ እያመጡ እንዳለ ይታያል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት የዩ ኤስ ኤይድ ኃላፊ ሳማታ ፓወር ናቸው፡፡ ኃላፏ ትህነግ ላይ ያልተጠበቀ አስተያየት ሰንዝረዋል።

አሸባሪው ህወሓት ከአፋርና አማራ ክልሎች በፍጥነት እንዲወጣ ጥሪ ከአንዴም ሁለቴ ጥሪ አቅርበዋል።  የኢትዮጵያና የቱርክ ትብብር መሰል ለውጦች እንዲመጡ በር ይከፍታል ተብሎ ይገመታል፡፡

ነገስ ምን ይፈጠር ይሆን? አብረን እናያለን!