“በዲጂታል ኢትዮጵያ” መርሃግብር ውስጥ የዲጂታል የጤና አገልግሎትን ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ኢትዮጵያ እየተሳተፈችበት የሚገኘው ዓለም አቀፉ የዲጂታል ጤና መድረክ “ለሁሉም የዲጅታል ጤና አገልግሎትን በማዳረስ የዲጅታል ጤና ማህበረሰብ ለመገንባት እና ፈጣን የጤና አገልግሎት መፍትሄ በመስጠት ማንም ወደ ኋላ እንዳይቀር ማድረግ” በሚል በበይነ መረብ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በፎረሙ ላይ የተሳተፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንግስት “በዲጂታል ኢትዮጵያ” መርሃግብር ውስጥ የዲጂታል የጤና አገልግሎትን ለመዘርጋት እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ለዲጂታል አሰራር ትኩረት ሰጥታለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣንና ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት ስርዓትን ለመዘርጋት ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።
አሰራሩን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችና እጥረቶችንም ለመድረኩ አብራርተዋል።
ከህዳር 28 እስከ 30 በሚካሄደው መድረክ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በበይነ መረብ እየተሳተፉ መሆናቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።