የጨረራና ኒዩኩሌር ቴክኖሎጂን ለማጎልበት እየተሰራ ነው – የኢትዮጵያ ጨረራ ባለስልጣን

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ፈርጀ ብዙ ችግሮችን የሚፈታውን የጨረራና ኒዩኩሌር ቴክኖሎጂ ለማጎልበት እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ ጨረራ ባለስልጣን አስታወቀ።
የጨረራና ኒዩኩሌር ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ ጥቅም በሚውሉ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ ነው።
የዓለም ሀገራት አሁን ለደረሱበት እድገት ቴክኖሎጂውን እንደ ዋነኛ አማራጭ እየተጠቀሙበት ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ከዘርፉ የሚገባትን አገልግሎት ለማግኘት በማለም ነው ባለስልጣኑን በአዋጅ በማቋቋም ወደ ትግበራ የገባችው።
የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌታቸው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፣ ቴክኖሎጂው በጤናው ዘርፍ ከምርመራ ጀምሮ የተሟላ ህክምናን እስከ መስጠት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ የማምረትና ሙሌት ልኬት፣ በመንገድ ስራ የኮንክሪት ጥቅጣቆ መጠን ልኬት እንዲሁም ለማዕድን እና ውሃ ዳሰሳ የሚያገለግል ቴክኖሎጂ መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ ሰለሞን አክለውም ቴክኖሎጂው በተለይም በግብርናው ዘርፍ ለገንዲ በሽታ ምክንያት የሆነውን የቆላ ዝንብ ለማምከንና ለምርጥ ዘር ብዜት ከፍተኛ ጥቅም ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።