ዩናይትድ ኪንግደም የኮቪድ-19 ክትባትን ዛሬ ለዜጎቿ መስጠት ትጀምራለች

ዩናይትድ ኪንግደም ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ዛሬ ለዜጎቿ መስጠት ትጀምራለች።
በመላው ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሚገኙ ከ70 በላይ የሚሆኑ ሆስፒታሎች እድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ ለሆኑ አዛውንቶች እና ለጤና ባለሙያዎች ክትባቱን ለመስጠት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
የአሜሪካ እና የጀርመን ኩባንያ የሆኑት ፋይዘር እና ባዮንቴክ ያበለጸጉት ክትባት ዩናይትድ ኪንግደም ለዜጎቿ እንዲሰጥ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን መፍቀዱ ይታወሳል። በዚህም ዩኬ ይህን ክትባት በመጠቀም የመጀመሪያዋ አገር ትሆናለች።
ክትባቱን ዛሬ ከሚወስዱት መካከል የ87 ዓመቱ ዶ/ር ሃሪ ሹክላ አንዱ ሲሆኑ ዶ/ር ሃሪ ክትባቱን ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ኒውካስትል በሚገኝ ሆስፒታል እንደሚወስዱ ገልጸው በዚህም ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የክትባት አሰጣጥ መረሃ ግብሩ ቅድሚያ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑትን በማስቀደም ሕይወት ወደቀደመ መልኩ እንድትመለስ ይረዳል ተብሏል።
“ቪ-ዴይ” ወይም የድል ቀን የሚል ስያሜ በተሰጠው ዕለት የሚጀመረው የክትባቱ መርሃ ግብር፤ ዜጎች ክትባቱን የመከተብ ግዴታ አይኖርባቸውም ተብሏል።