ይድረስ ለመርካቶ

በቅድሚያ፣ ለዚያ ለፍቶ ጥሮ አዳሪ የመርካቶ ወገኔ፣ ከልቤ የተሰማኝን ሀዘን ለመግለፅ እወዳለሁ።
መርካቶን በልኩ ለተረዳ፣ አይደለም እንዲህ ያለው ሰፊ ውድመት፣ የአንዲት ጉልት መቃጠል፣ ለመርካቶ በጣም ብዙ ማለት ነው።
አንዲት ጉሊት፣ ትዳር ታስይዛለች፣ አንዲት ኪዮስክ፣ ቤተሰብ ታሰተዳድራለች፣ እቁብ ትጥላለች፣ እድር ትከፍላለች፣ የብዙ ሰው ህይወት ነች።
መርካቶ የሁላችንም ህይወት ነው።
ጉሮሮ ነው
ተስፋ ነው
ብዙ ነገራችን ነው።
በውድመቱ ለተጎዱ ሁሉ፣ ሀዘናችንን እንገልፃለን።
ለተጎዱት መፅናናትን ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉም፣ ለአስፈላጊው ትብብር፣ ከጎናቸው እንዲቆም እመኛለሁ።
ከምንም በላይ ደግሞ፣ “ቀጣይ እርምጃችን ምን ይሁን?” ብለን እንጠይቅ።
‘What’s Next?’
እሳቱ፣ በቁጥጥር ስር ውሏል!
በእሳቱ የተጎዳ ህዝብ አለ።
የተጎዳው ወገናችን፣ የደረሰበትን ውድመት፣ የጠፋውን ሀብት ለማስላት፣ የተረፈውን ሰብስቦ ለማስቀመጥ፣ እንደገና ለመደራጀት፣ እንደገና ወደ ስራ ለመመለስ፣ እየታገለ ነው። በጉልበት፣ በገንዘብ፣ በፀሎት፣ በሞራል…እናግዘው። ለወገን መድኃኒቱ ወገን መሆኑን በተግባር እናሳይ።
ከዚህ ጎንለጎን በችግሮቻችን ለመቆመር የሚታገሉትን በጥንቃቄ እናስተውል።
ንብረታቸው የተቃጠለባቸውን ወገኖች ለማትረፍ የተሯሯጠ ወገን እንዳለ ሁሉ በእሳቱም ለመጠቀም የተሯሯጠ ጉደኛም አለ። ክፉውን አጋጣሚ ተጠቅሞ የህዝብን ንብረት ብቻ ሳይሆን፣ የህዝብን ሰላም ለመዝረፍ የተሯሯጠም አለ።
ሌላ ትግል ውስጥ ያሉም አሉ፣ እሳቱ አልጠፋም የሚሉ፣ እሳቱ ሆን ብሎ የተለኮሰ ነው፣ ከተማዋን ለማውደም የተጫረ ነው፣ ህዝቡን ከእነ ንብረቱ ለማጥፋት የተለኮሰ ነው ወዘተ የሚሉ።
የእሳት አደጋ በደረሰ ጊዜ ሁሉ፣ የእሳት አደጋ ነጋዴዎች ይፈጠራሉ፣ በእኛ አገር ብቻ አይደለም! በዚህ ዘመን ብቻም አይደለም!
ቁጭራ ሲቃጠል፣ የአጼው መንግስት፣ ሰዎቹን ለማስነሳት ፈልጎ አቃጠለው ተብሏል።
ጆኒያ ተራ ሲቃጠል፣ ደርግ ቦታውን ፈልጎት ነው ተብሏል።
ድሬደዋ ታይዋን ሲቃጠል፣ ኢህአዴግ ንግዱን ከአንድ ወገን ለመንጠቅ የለኮሰው እሳት ነው ተብሏል። ሌላም ብዙ ማሳያ መዘርዘር ይቻላል።
እሳት አደጋ ደርሶ፣ እገሌ ነው! ይህን ፈልጎ ነው። ያቃጠለው ያልተባለበት ጊዜ የለም።
በውጭም አገር እንዲሁ ነው።
ወረርሽኝ ሲመጣ፣ መንግስት የህዝቡን ቁጥር ለመቀነስ፣ ጥቁሮችን ለመፍጀት፣ ላቲኖዎችን ለማጥፋት፣ አንድን ቡድን ለማሸማቀቅ፣ ወዘተ ነው የሚሉ የፖለቲካ ዘማቾች፣ ከወረርሽኙ ጋር ይፈለፈላሉ።
“Conspiracy theorists” ይባላሉ፣ ለእነዚህ ዘማቾች፣ እሳት ይምጣ፣ በሽታ ይነሳ፣ ፍንዳታ ይድረስ፣ ይህ ሁሉ፣ መንግስት፣ ወይም የተወሰኑ ሀብታሞች፣ የተወሰኑ ፖለቲከኞች የጠነሰሱት ሴራ ነው!
ለወረርሽኑ፣ መድሀኒት አትውሰድ ይሉሀል! ክትባት አትወጋ! እንደ በሽታው ሁሉ፣ መድሀኒቱም፣ ክትባቱም ሴራ ነው ይሉሀል! ለበሽታው መድሀኒት የላቸውም! ለፍንዳታው መልስ የላቸውም! ለእሳቱ ማጥፊያ የላቸውም!
የመርካቶ ሌባ በግርግሩ መሀል፣ እቃ ሰርቆ መጠቀም ይፈልጋል
የፖለቲካ ሌባ፣ በግርግሩ መሀል፣ የሰውን ሀሳብ፣ የሰውን ሰላም ሰርቆ፣ ህዝብን ማምታታት፣ አገርን መጉዳት ይፈልጋል፣ አገር ስትጎዳ፣ የሚጠቀም ይመስለዋል፣ አገር ብትሸነፍ፣ ጠላቱን ያሸነፈ ይመስለዋል
የሴራ አርበኞች፣ በየትም አገር እንደዚሁ ናቸው፣ በየትኛውም ዘመን ያው ናቸው!
የሚገዳቸው፣ እውነት አይደለም፣ ወድያው የሚያገኙት ጥቅምም የለም፣ የእነሱ ጥቅም፣ አገር ላይ ቀውስ መፍጠር፣ ህዝብ መሀል ውዥንብር መፍጠር ነው።
ሴራውን ለሴረኞች ትተን፣ ወደ መርካቶ እና ወደ ኑሮአችን በመመለስ፣ መጠየቅ ያለብንን ጥያቄ እንጠይቅ!
እሳቱ ለምን ተነሳ?
ከየት ተነሳ?
ምን ያህል ጥፋት ደረሰ?
የሚጠየቅ ሰው ወይም አካል አለ?
የተጎዱትን እንዴት መርዳት ይቻላል?
እንዲህ አይነቱ አደጋ እንዳይደርስ ወደፊት ምን ማድረግ አለብን?
እነዚህን መመለስ፣ ይበልጥ ያራምደናል!
ከጥንቃቄ በተጨማሪ ዘመናዊነትም አይለየን፡፡
በዚህ እሳት ክፉኛ እና በቀላሉ የተጎዳነው፣ አንድም፣ ዘመናዊ ከተማ ስለሌለን ነው።
ቤቶች፣ በፕላን እና በጥራት በተሰሩባት ከተማ፣ እንዲህ አይነት አደጋ የመድረስ እድሉ፣ ዝቅተኛ ነው። ህንጻዎች በፕላን እና በጥራት በተሰሩባት ከተማ ፣ ሰፋፊ መንገዶች በተሰሩላት ከተማ፣ መግቢያ መውጫው፣ ተለይቶ በሚታወቅ ከተማ፣ እንዲህ አይነቱን አደጋ በቀላሉ መቆጣጠር ይቻላል። በፕላን እና በጥራት በተሰራ ከተማ ፣ አደጋ ሲደርስ፣ ወንጀልን በተሻለ ቅልጥፍና መከላከል ፣ መተባበር ፣ መረዳዳት፣ የተጎዱትን ማሳከም፣ ማቋቋም ይቀላል። የጠፋውን ቶሎ እንተካ፣ የተጎዱትን እናግዝ! ከሁሉም ከሁሉም በላይ፣ ከተማችንን እናዘምን! በሴራ ሳይሆን፣ በምክንያት እንኑር!
በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ፣ አሜሪካ ውስጥ፣ ሰዎችን መሰለል ስለበዛ፣ ነዋሪውም ስለተማረረ፣ አንድ የሴራ ጥንቆላ-ወ-ሳይንስ ተለቀቀ፡፡ እዚህ ሰማዩ ላይ፣ ከበላያችን የሚበሩት፣ ወፎች አይደሉም፣ መንግስት ወፎቹን በሙሉ አጥፍቶ፣ በስለላ ድሮን ተክቷቸዋል ተባለ፡፡ አሁን ከበላያችን የሚበሩት፣ ወፎች ሳይሆኑ፣ ድሮኖች ናቸው የሚል ተውኔት ተጽፎ፣ ብዙ አማኞች አገኘ፡፡ ሳይንሱ፣ ጥንቆላ መሆኑ ታውቆ፣ መሳቂያ እስኪሆን ድረስ፣ በርካቶችን አሞኝቷል፡፡
ወደ ቅርቡ ዘመን ስንመጣ ደግሞ፣ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ አለምን በተለይም አሜሪካን ባራወጠበት ጊዜ፣ ኮቪድን የሚያስከትለው፣ 5G ቴክኖሎጂ ነው የሚል ተረት ወይም ጥንቆላ ተጀመረ፡፡ የሰውን የተፈጥሮ መከላከያ አዳክሞ፣ ህዝባችንን ለወረርሽኙ የዳረገው፣ የ5G ኔትወርክ ነው ብሎ አምኖ፣ አንዳንዱ ሰው፣ መንግስትን ክፉኛ ተቃውሞ ተነሳ፡፡ አንዳንዱ አሜሪካዊ፣ የቴክኖሎጂውን ተሸካሚ ምሰሶዎች፣ መሰባበር፣ ማፈራረስ ጀመረ፡፡ የእኛም አገር የፖለቲካ ጠንቋዮች፣ ከእነዚህ የሚለዩት፣ በቀለም እና በዜግነት ብቻ ነው
ጎበዝ፣ ጊዜ የለም፣ እነሱ ይጠንቁሉ!
እኛ፣ የፈረሰውን ገንብተን፣ ሩጫችንን እንቀጥል
ጋዜጠኛ መሀመድ ሀሰን
የዋልታ ሚዲያና ኮምኒኬሽን ኮርፖሬት
ዋና ስራ አስፈፃሚ