ዳሞታ ተራራ – የወላይታ ሶዶ ውበት

ዳሞታ ተራራ

የዳሞታ ተራራ ከወላይታ ሶዶ ከተማ በስተሰሜን የሚገኝና በደን የተሸፈነ የብዘሃ ህይወት አለኝታ ነው። ተራራው ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው መስህብ ስፍራዎች የሚገኝበት ነው።

በሀገር በቀል ዕፅዋት የተሸፈነና አረንጓዴ ሸማ የለበሰው ይህ ተራራ በክፍታውና በግርማ ሞገሱ ወደ ከተማዋ የሚገቡትን ጎብኚዎች ቀልብ በመግዛትም ይታወቃል።

ተራራው የሚሸፍነው መሬት 12 ሺሕ 500 ሄክታር ሲሆን ከፍታው ከባህር ጠለል በላይ 3 ሺሕ ሜትር ነው። ዙሪያው 68 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት እንዳለውም ይነገራል።

የዳሞታ ተራራ በወላይታ ሕዝብ ዘንድ በዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የሚታወቅ ታሪካዊ ስፍራ ሲሆን ከህዝቡ ታሪክና ባህል እንዲሁም ጀግንነት ጋር በማቆራኘትም ዳሞታን በሥነ ቃላቸው ያሞጋግሱታል በሙዚቃዎቻቸውም ታሪኩን ያወሣሉ።

ተራራው ከልምላሜው፣ ከዱር እንስሳትና ተፈጥሯዊ ብዝሃ ህይወት ማህደርነት ባሻገር በወላይታ ዞን የሚገኙ ወረዳዎች ስያሜዎቻቸውን ዳሞታን መነሻ አድርገው ይጠሩታል፡፡ ከእነዚህም ወረዳዎች ዳሞት ሶሬ፣ ዳሞት ወይዴ፣ ዳሞት ጋሌ እና ዳሞት ፑላሳ የሚጠቀሱ ሲሆን ለተለያዩ ቀቤሌዎችም የመጠሪያቸው መነሻ ነው የዳሞታ ተራራ፡፡

የዳሞታ ተራራ ለከርሰ-ምድርና ገጸ-ምድር ውሃ መበልጸግና መበራከት ከፍተኛ ሚና ያለው የብዙ ምንጮችና ጅረቶች ምንጭ ነው፡፡ ከተራራው መነሻቸውን አድርገው የሚፈሱ ወንዞችም ቁጥር ብዙ ሲሆን 32 ምንጮችና 12 ጅረቶች የተራራው ገጸ-በረከቶች እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በተጨማሪም የወላይታ ሶዶ ከተማን በከፊል የሚያጠጣው የንፁህ የመጠጥ ውሃ የሚገኘውም ከዚሁ ተራራ ነው፡፡ ከከተማዋ ሆነው ሲመለከቱት ቀልብን የሚስብ እይታ ያለውና ለከተማዋ ግርማ ሞገስና ውበት ያላበሰ የከተማዋ የመስህብ ተራራም ነው ዳሞታ፡፡

የዳሞታ ተራራ ጥንታዊ የወላይታ ነገስታት መናገሻና ታሪካዊ ስፍራ ሲሆን በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ዋሻዎች እና የተለያዩ የተፈጥሮና የሰው ሠራሽ የቱሪስት መስህቦች የሚገኙበት ነው፡፡

በተራራው ከአምስት በላይ የተፈጥሮ ዋሻዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መስህቦች መካከል የጥንታዊ “ሞቼና ቦራጎ” ዋሻ አንዱ ነው። ጥንት በዋሻው ሰዎች ይኖሩ እንደነበረም ታሪክ ያስረዳል። ዋሻው በውስጡ ከአምስት መቶ በላይ ሰዎች የመያዝ አቅም እንዳለውም ይነገራል፡፡ ስፋቱ 38 ሜትር ሲሆን የጣሪያው ከፍታ 33 ሜትር እንዲሁም የዋሻው ዙሪያ ልኬት ደግሞ 58 ሜትር መሆኑንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ዳሞታ ተራራ የተለያዩ መስህቦች ባለቤት ሲሆን የነገስታት መኖሪያ ሥፍራዎች፣ ፏፏቴዎች፣ ደብረ-መንክራት አቡነ ተክለኃይማኖት ገዳምን ጨምሮ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትና አድባራት የሚገኙበትና ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻም ነው፡፡
ወላይታ ሶዶን ይጎብኙ አገርዎን ይወቁ!! ቸር እንሰንብት!!

በሠራዊት ሸሎ