መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የጤና ሚ/ር ዴኤታ ወ/ሮ ሰሀረላ አብዱላሂ እና ሌሎች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በትግራይ ክልል የመቐሌ አጠቃላይ ሆስፒታልን እና በህግ ማስከበሩ ወቅት የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጎብኝተዋል፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የጤና ቢሮ ኃላፊዎች እና ከፌደራል ተመድበው እየሰሩ ካሉ ባለሞያዎች ጋር የድንገተኛ ምላሽ እና መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ለማጠናከር እየተሰሩ ባሉት ስራዎች ዙሪያ መክረዋል፡፡
በዚህም የጤና አገልግሎቶችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ከማደረግ አኳያ እና ለተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጠው የህክምና አገልግሎቶች እንዲጠናከር የባለሞያ፣ የሕክምና ቁሳቁስ፣ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚቀጥልና በተለይም ከሌሎች ሴክተሮችና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ መስራት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ሚኒስትሯ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደሩ የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፋሲካ አምደስላሴም እየተደረገ ያለው ሁሉ አቀፍ የጤና ሚኒስቴር ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
መንግስት ሕዝቡን ለመድረስ እያደረገ ያለውን ጥረት እየደገፉ ያሉ አጋር ድርጅቶች፤ የተለያዩ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ሚኒስቴሩ አመስግኖ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡