ጋራምባ ተራራ – የውብ ተፈጥሮ መስህብ ሥፍራ

ጋራምባ ተራራ

ጋራምባ በሲዳማ ክልል በደጋማው አከባቢ የሚገኝ እና በውብ የተፈጥሮ ጸጋ የታደለ ተራራ ነው። በክልሉ በርዝመት ቀዳሚ ከፍተኛ ሥፍራ ሲሆን ከባህር ጠለል በላይ 3 ሺሕ 368 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል።

ተራራው ከክልሉ ዋና መቀመጫ ሀዋሳ ወደ ደቡብ ምስራቅ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከአዲሰ አበባ ወደ ተራራው ለመድረስ ደግሞ 365 ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ።

በሀገር በቀል ጥብቅ የተፈጥሮ ደን የተሸፈነ፣ በደጋ ቀርቀሃ የደመቀና ልብን በሚማርክ መልክአ ምድር የተሞሸረ እና በብዝሀ ህይወት ስብጥር የታደለ ውብ የቱሪዝም መዳርሻ ነው የጋራምባ ተራራ።

የተራራው ስነምህዳር ምቹ በመሆኑ የተለያየ ዝርያ ያላቸው የዱር እንስሳት ተራራውን መኖሪያቸው አድርገዋል፡፡ በተራራው ነብር፣ አቦ ሸማኔ፣ ቀበሮ፣ ባለ ነጠብጣቡ ጅብ እንዲሁም የተለያዩ የድኩላ እና ሌሎች የእንስሳት ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡ የተለያዩ የአዕዋፋት ዝርያዎችንም በተስማሚው አየሩ አቅፎ ይዟል።

ብዝሃ ዝርያ ያላቸው የዕፅዋት ክምችት ባለቤት እና የበርካታ የሀገር በቀል ዛፎች መገኛም ነው ጋራምባ።

ተራራው ወደ 100 የሚጠጉ ወንዞችና ጅረቶች መፍለቂያ ሲሆን የውሀ ማማ ተብሎም ይሞገሳል። የጊዳዎ፣ የገላና፣ የገናሌ እና ሌሎች ወንዞች መነሻቸው ከዚሁ ከጋራምባ ተራራ ነው፡፡ በርካታ የተፈጥሮ ፍል ውሃዎች እንደሚገኙበትም መረጃዎች ያሳያሉ።

የጋራምባ ተራራ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዛ ሲፍራ ሲሆን ለተራራ የእግር ጉዞም ተመራጭ ነው፡፡ ከተራራው አናት ሆነው የሲዳማ ክልል አከባቢዎችን እና ሌሎች አከባቢዎችን በርቀት እስከ ዕይታዎ ጥግ ማየት ይችላሉ፡፡ በመልክአ ምድር አቀማመጥና በተፈጥሮ ውበትም ይደነቃሉ፡፡ የተለያዩ ሀገር በቀል ዕፅዋትን፣ አእዋፋትን እንዲሁም በተራራው ዙሪያ የሚርመሰመሱ የዱር እንስሳትን ለመጎብኘት የሚያስችል የቱሪዝም መዳረሻ ነው፡፡

ወደ ተራራው ሲጓዙ ከውብ መልክአ ምድር አቀማመጥና ከተፈጥሮ ውበት ጋር ተዳምሮ ደምቆ የሚታየው የሲዳማ ባህላዊ ቤቶች አሠራር ውስጥን ይማርካል፡፡ የአከባቢው ህብረተሰብ እንግዳ ተቀባይነት ደግሞ ሌላው ትልቅ የሲዳማዎች የቆዬ እሴት በመሆኑ ጎብኚው በጉዞው ተደስቶ የሚመለስበት አከባቢ ነው፡፡

ታዲያ በብዝሃ ህይወት ስብጥር የታደለው የጋራምባ ተራራ የማህበረሰብ ጥብቅ ቦታና አከባቢው የማህበረሰብ አቀፍ ተሪዝም መዳረሻ ሆኖ እየለማ እንደሚገኝ የተለያዩ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

አከባቢው በቱሪስት መስህብ ይዘቱና እየለማ ካለው የማህበረሰብ አቀፍ ተሪዝም ልማት መነሻ የዓለም ምርጥ የቱሪስት መንደር (world best tourist Village) ሆኖ ለመመዝገብ መታጩቱን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከዚህም ባሻገር የሲዳማ ክልል በርካታ እምቅ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም መደረሻዎች የሚገኝበት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሲዳማን ይጎብኙ ሀገርዎን ይወቁ!!
ቸር እንሰንብት!!

በሠራዊት ሸሎ