ጨበራ ጩርጩራ – የብዝኃ መስህብ መገኛ

ጨበራ ጩርጩራ

የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ በተፈጥሮ ሁሉንም የታደለ ድንቅ የመስህብ ሥፍራ ሲሆን በደቡበ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በዳውሮ እና ኮንታ ዞኖች መካከል በ1997 ዓ.ም የተቋቋመና የቆዳ ስፋቱም 1 ሺሕ 410 ስኩዌር ካሬ ኪሎ ሜትር ነው።

ከአዲስ አበባ 450 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውና ውብ ተፈጥሮን የተቸረው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ጥቅጥቅ ደን፣ ክረምትና በጋ ሳያቋርጡ የሚፈሱ ወንዞችና ጅረቶች፣ ልብን የሚማርኩ ሀይቆች፣ ፏፏቴዎች እንዲሁም የፍል ውኃዎች መገኛ ነው።

በገጸ ምድር የውሃ አካላት ውበትን የተጎናጸፈው ይህ ሥፍራ 50 የሚሆኑ ወንዞችና ጅረቶች ባለቤት ነው። አምስት የተፈጥሮ ሀይቆችም በፓርኩ ውስጥ ይገኛሉ።

በረጃጅም እና በለምለም ሣር የተሸፈነው አስደናቂው የፓርኩ ተፈጥሮ ለዱር እንስሳት ምቹ መኖሪያ ሆኖላቸዋል። የአፍሪካ ዝሆን፣ ጎሽ፣ እንበሳ እና ነብርን ጨምሮ 57 የተለያዩ ዝርያ ያላቸው አጥቢ የዱር እንስሳት መገኛ መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ብሔራዊ ፓርኩ ከ137 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎችን አቅፎ የያዘና ከነዚህም ውስጥ ስድስቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው።

በተፈጥሮ ውበትና በብዝኃ ህይወት ስብጥሩ የታደለው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ከ106 በላይ የሚሆኑ የዕፅዋት ዝርያዎች በውስጡ እንደሚገኙም ጥናቶች ያሳያሉ። በተራሮች፣ በሸለቆዎች፣ በወንዞች፣ በፏፏቴዎች፣ በፍል ውኃዎች፣ በዋሻዎች እና በሀይቆች የተሸላለመው ብሔራዊ ፓርኩ ብርቅዬ የአዕዋፍና የዓሣ ዝርያዎች የሚገኙበትም ነው፡፡

በልምላሜውና በአረንጓደው መስኩ ለተለያዩ እንስሳት ምቹ መኖሪያ በመሆን ዝናን የተቀዳጀው ይህ የመስህብ ሥፍራ የጎብኚዎችን ቀልብ በመግዛትም ይታወቃል፡፡ የተራራው እና የጋራ ሸንተረሩ ውበት፣ በጥቀጥቅ ደን ውስጥ የሚርመሰመሱ የዱር እንስሳትና የአእዋፍት ብዛት ብሎም የዕጽዋት ክምችቱ እምቅ የቱሪዝም መዳረሻነቱን ያስመሰከሩ የፓርኩ ጸጋዎች ናቸው፡፡

ታዲያ ይህን ውብ ተፈጥሮ የታደለው የቱሪዝም መዳረሻ እንደእምቅ ጸጋው ሳይለማና በቱሪዝም ዘርፍም ማግኘት የሚገባውን እድል ሳይጠቀም የኖረ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

ይሁን እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተጀመረው “ገበታ ለሀገር” እሳቤ ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለማልማት ሰፊ ዕድል ፈጥሯል፡፡

በዚህም የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ በ“ገበታ ለሀገር” ከለሙት የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዱ ሲሆን የኮይሻ ፕሮጀክት አካል ሆኖ በመልማቱ አሁን እምቅ ጸጋውን የሚመጥንና ደረጃውን የጠበቁ የቱሪስት ማረፊያዎች እንዲሁም ምቹ መሠረተ ልማት በማሟላት ለጎብኚዎች ምርጥ የቱሪዝም ስበት ማዕከል ወደመሆን ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን ይጎብኙ አገርዎን ይወቁ!!

በሠራዊት ሸሎ