ኢሰመኮ በምርጫ ሊተገበሩ ይገባል ባላቸው የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፃ እያደረገ ነው

ዶ/ር ዳንኤል በቀለ

ግንቦት 23/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምርጫ 2013 ሊተገበሩ ይገባል ባላቸው ባለስድስት ነጥብ የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፃ እያደረገ ነው።

ኮሚሽኑ ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያዘጋጀውን ባለስድስት ነጥብ የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ማስተዋወቅን ታላሚ ያደረገ የዐውደ ምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ ከምርጫው በፊት፣ በምርጫው እለትና ከምርጫ በኋላ ባሉ የምርጫ ሂደት የሰበዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ ክትትልና ግምገማ ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

ኮሚሽኑ ያዘጋጀው የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳዎችም ተጨባጭ የሰብዓዊ መብቶች እርምጃዎች ቃል ኪዳን፣ ለሰብዓዊ መብቶች በቁርጠኝነት መቆም፣ ምርጫው ለስርዓተ-ፆታ ምላሽ ሰጪ መሆኑን ማረጋገጥ፣ የህግና ፖሊሲዎች ማሻሻያ ቃል ኪዳን፣ የመንቀሳቀስ፣ የመደራጀት፣ መረጃ የማግኘትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ማረጋገጥ እና ለግጭት ቀስቃሽና የጥላቻ ንግግር እንዲሁም ከኃይል እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ መቆጠብ መሆናቸው ተገልጿል።

(በደረሰ አማረ)