ኢትዮጵያውያን የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በጣሊያን ሮም ሰልፍ አካሄዱ

በጣሊያን ሮም ኢትዮጵያውያን ሰልፍ

ግንቦት 23/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመንግስትን አቋም በመደገፍ የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለውን ጣልቃ ገብነትና ጫና በመቃወም ሰልፍ አካሂደዋል።

ሰልፈኞቹ የግብፅና ሱዳንን የሴራ አካሄድ የተቃወሙ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት አቋም በመደገፍ በጣሊያን ሮም ከተማ ሰልፍ አድርገዋል።

ሰልፈኞቹ አሜሪካ በኢትዮጵያና በኤርትራ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት፣ የሱዳንን የድንበር ወረራ እና በህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ሱዳን እና ግብፅ እየሄዱበት ያለውን ሴራ አውግዘዋል።

እንዲሁም የምዕራባዊያን ሚዲያዎችን ከኢዲቶሪያል ፖሊሲ ያፈነገጠ ዘገባ ተቃውመዋል።

አሁን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ከምዕራባውያን ጫና ሳይሆን ለተፈናቀሉ እና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች እገዛ የሚፈልጉበት ወቅት መሆኑን በአፅንዖት ገልፀዋል።

በተጨማሪም የህዳሴ የግድብ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት በተያዘለት እቅድ መሰረት እንዲካሄድና ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ ገልፀዋል።

የህወሃት የጥፋት ቡድን አሁንም ከአንዳንድ የውጭ የጥፋት ሽሪኮቹ ጋር በመሆን የተካነበትን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ጫና ለመፍጠር የሚችለውን እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰልፈኞቹ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመቀነስ፣ ሰብዓዊ እገዛ ለማድረግ እና አገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል እንዲሁም የአገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉም በያሉበት ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ከሰልፉ ጎን ለጎን ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ አስር ሺህ ዩሮ ለግድቡ የቦንድ በመግዛት አጋርነታቸውን ገልጸዋል።