ግንቦት 28/2013 (ዋልታ) – በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በምስራቅ ወለጋ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ግንባታዎችን አስመረቁ።
በሶስት ወረዳዎች የተገነቡ ፕሮጀክቶች የንፁህ መጠጥ ውሀና የድልድይ ግንባታዎች ሲሆኑ ነዋሪዎቹ ከዚህ ቀደም በነዚህ የመሠረተ ልማት እጥረት ሲቸገሩ እንደነበር ተነስቷል።
በተለይም የመንገድ እና የድልድይ መሠረተ ልማቶች ባለመኖራቸው የአከባቢው ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ጫና ሲፈጥር እንደነበር ነዋሪዎቹ አንስተዋል።
ምንም እንኳን አከባቢው ላይ የተለያዩ የቅባት እህሎችና ሌሎች የግብርና ምርቶች የሚመረትበት ቢሆኑም አርሶአደሮች ያመረቷቸውን ለገበያ እንዳያቀርቡ እንቅፋት ነበር ነው የተባለው።
በባለፈው የበጀት ዓመት የክልሉ መንግስ 90 ድልድዮችን ብቻ ለአገልግሎት ማድረጉን ያስታወሱት ዶ/ር ግርማ በዘንድሮው ዓመት በተሻለ የስራ አፈፃፀም 160 ድልድዮች ደረጃቸውን ጠብቀው መገንባታቸውን አንስተዋል።
በወረዳው በሲቡ ቡሬና ሙጤ ከተማ እና አኖ ቦሼ አከባቢ ላይ የተገነቡ ድልድዮች በአጠቃላይ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው ሲሆን ርዝመታቸውም ከ7 ሜትር በላይ ናቸው።
ድልድዮቹ አከባቢውን ከተለያዩ አጎራባች ወረዳዎች ጋርም በማገናኘት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴውን ያሻሽላልም ነው የተባለው።
በሌላ በኩል በአኖ ቦሼ ላይ የተገነባው የንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ሲሆን ሁለት ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ በማካሄድ የተገኘ የከርሰ ምድር ውሃ ነው።
ፕሮጀክቱ 300 ኪዩቢክ ሜትር ውሃን የሚችል ማጠራቀሚያን ጨምሮ ጄኔሬተር እና የሰራተኞች መኖሪያን ያጠቃለለ ነው።
ዶ/ር ግርማ አመንቴ አክለውም የክልሉን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እና ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ እና የሰው ወደ ልማት በማስገባት አገራዊ ጥቅሙን ከፍ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰቶ ይሰራል ብለዋል።
(በሚልኪያስ አዱኛ)