በምዕራብ ወለጋ ዞን ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑ ተገለጸ

ሰኔ 05/2013 (ዋልታ) – በምዕራብ ወለጋ ዞን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ከአንድ ሺህ 600 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከፀጥታው አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኤሊያስ ኡማታ ለዋልታ እንደገለጹት ዞኑ 23 ወረዳዎች ያሉት ሲሆን ከምርጫ በፊት የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን በተመለከተ የምርጫውን ሰላም ለማስጠበቅ፣ የህዝቡን ግንዛቤ ለመጨመር እና የምርጫ አሰፈፃሚዎችን አቅም ለማጎልበት በምርጫ ቦርድ መስፈርት መሰረት በቂ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁሟል።

በዞኑ ከሚገኙት 11 የምርጫ ጣቢያዎች መካከል ዘጠኙ ምርጫ ለማካሄድ መስፈርቱን ያሟሉ ተብለው በምርጫ ቦርድ የተመረጡ ሲሆን ቀሪዎቹ መስፈርቱን አሟልተው ባለመገኘታቸው ምርጫው አይካሄድባቸውም።

በአጠቃላይም በዞኑ ካሉ ወረዳዎች ሲታይ ከ23ቱ መካከል በ19 ጣቢያዎች ምርጫ ይካሄዳል ተብሏል።

በሀገሪቱ የፀጥታ ችግር ከነበረባቸው አካባቢዎች ምዕራብ ወለጋ አንዱ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ የፀጥታው ችግር እየተቀረፈ እንደማንኛውም የሀገሪቷ ክፍል ለስድስተኛው ምርጫ መዘጋጀት ብቻ ሳይሆን የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

(በሚልኪያስ አዱኛ)