ባለስልጣኑ ከማስታወቂያ ባለሙያዎች ጋር እየተወያየ ነው

ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ከማስታወቂያ ባለሙያዎች ጋር የጋራ ምክር ቤት ለማቋቋም ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ ኢድሪስ ከዚህ ቀደም የማስታወቂያ ባለሙያዎች ተሰባስበው በጋራ የሚንቀሳቀሱበት ምቹ ሁኔታ እንዳልነበር ገልጸው ባለስልጣኑም ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ሰጥቶ ስላልነበር  ከዘርፉ መገኘት ያለበትን ገቢ ሀገሪቱ እንዳላገኘች ተናግረዋል፡፡

የማስታወቂያ ባለሙያዎች የጋር ምክር ቤቱ መቋቋሙ ሙያተኞች በጋራ ተቀናጅተው እንዲሰሩ እና ዘርፉን ከማነቃቃት አንፃር ሚናው የጎላ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

የጋራ ምክክር ቤቱ ማቋቋሚያ ኮሚቴ አባል ዳንኤል ብርሃኑ በበኩላቸው ዘርፉ ምንም ዓይነት የስነምግባር መርህ የማይከተል እንደነበር አስታውሰው የሚተዳደርበት ደንብ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

የመተዳደሪያ ደንቡም በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት፣ ለአሰራር ምቹ ሜዳን መፍጠር፣ በማስታወቂያ ባለሙያዎች እና በህብረተሰቡ መካከል መተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መፍጠርን ዓላማ አድርጎ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

የማስታወቂያ ስራን ጥራት ለመመዘን የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እና ሙያተኞችን ማብቃት ላይ የጋራ ምክር ቤቱ ትኩረት አድርጎ ይሰራል ተብሏል።

በመድረኩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የማስታወቂያ ባለሙያዎችም የጋራ ምክር ቤቱን ለማቋቋም በሚያስችሉ ሁኔታዎች እና በቀረበው የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን አንስተዋል።

(በትዕግስት ዘላለም)