የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ከ3.4 ሚሊየን ቶን በላይ የወጪና ገቢ እቃዎችን ማጓጓዙ ተገለጸ

ሰኔ 11/2013 (ዋልታ) – የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አክሲዮን ማህበር ባለፉት ሶስት ዓመታት ከሶስት ነጥብ አራት ሚሊየን ቶን በላይ የወጪና ገቢ ዕቃዎች ማጓጓዙን አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሰርካ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ በመጀመሪያ ዓመት ስምንት መቶ ሺህ፣ በሁለተኛ ዓመት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን፣ በሶስተኛ ዓመት አንድ ነጥብ 45 ሚሊየን ቶን እቃ ማጓጓዝ ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከሶስት ነጥብ 45 ሚሊየን ቶን በላይ ዕቃ አጓጉዟል ብለዋል፡፡

በዚህም የወጪና ገቢ እቃዎች እድገት ማሳየቱን ጠቁመው፣ አገልግሎት አሰጣጡም በየአመቱ ከ25 እስከ 30 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና የሶስት ዓመታት ጉዞውም ጤነኛና ስኬታማ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

የልማት መሳሪያዎች፣ የንግድ ሸቀጦች፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት አግልግሎት ድርጅትና የግሉ ዘርፍ በኮንቴነር የሚያስመጧቸውን ሸቀጦች በማጓጓዝም ስኬታማ እንደነበር አመልክተዋል፡፡

የባቡር አገልግሎት ፋይዳ እየሰፋ በመምጣቱ የወጪና ገቢ ንግዳችንን በማሳለጥ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ያሉት ኢንጂነር ጥላሁን፣ ተደራሽነቱን ለማስፋት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ እያመጣን ነው ብለዋል፡፡ ከጭነቱ ጎን ለጎንም የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን ሲሉም አክለዋል፡፡

በኮቪድ-19 ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት በተወሰነ መልኩ መስተጓጓሉን ጠቁመው፣ አሁን የትራንስፖርት አገልግሎቱ በድጋሚ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡