በምርጫ ወቅት የሕግ አስከባሪ አካላት ሰብአዊ መብቶችን አክብረው መንቀሳቀስ አለባቸው – ኢሰመኮ

ሰኔ 11/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በምርጫ ወቅት የሕግ አስከባሪ አካላት ሰብአዊ መብቶችን አክብረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳሰበ፡፡

ኮሚሽኑ በምርጫ ሂደት የሰብአዊ መብት ጥበቃን በሚመለከት ምርጫ በሚካሄድባቸው ሁሉም ክልሎች ከሕግ አስከባሪ አካላት እና አመራሮች ጋር  ምክክሮችን አከናውኗል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የሕግ አስከባሪ አካላት ሰብአዊ መብቶችን አክብረው ተግባራቸውን ለማከናወን የገቡትን ቃልኪዳን በምርጫው ሂደት በተግባር በመተርጎም የምርጫ ሂደቱ ሰብአዊ መብቶች የተረጋገጡበት እንዲሆን በቁርጠኝነት መስራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የሕግ አስከባሪ አካላት ካለባቸው ሰብአዊ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት ኃላፊነት አኳያ፣ በቅድመ ምርጫው፣ በምርጫው ዕለትና በድኅረ-ምርጫው ወቅት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ የሕግ አስከባሪ አካላትን ግዴታና ኃላፊነቶች ለማስታወስ ያለሙ ናቸው ተብሏል፡፡

በተለይም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመዘዋወር፣ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶችን ጨምሮ ሌሎች በምርጫ ወቅት ትኩረት የሚሹ ሰብአዊ መብቶችን በማረጋገጥ ረገድ የሕግ አስከባሪ አካላት ሚና በዝርዝር ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ኢሰመኮ በምርጫው ወቅት የሕግ አስከባሪ አካላት በገለልተኝነት ተግባራቸውን በመወጣት የዜጎች መብቶችን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ እንዲሁም ጥሰቶች ሲኖሩ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ  አሳስቧል።

የሕግ አስከባሪ ተቋማት ባልደረቦችም ተግባራቸውን ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ ለማከናወን ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።