የመንግስት ልዑክ ቡድን ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቀና

ሰኔ 11/2013(ዋልታ) – በሳዑዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ባለው ወቅታዊ ችግር ላይ ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር ለመነጋገር ፤ኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ዛሬ ወደ ስፍራው መላኳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተላከው ልዑክ በሳዑዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ለሚመለከታቸው የሳዑዲ መንግስት አካላት እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል በሚደረገው ውይይትና ምክክር ላይ ያለ ህጋዊ ፍቃድ በሀገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የጉዞ ቅድመ-ሁኔታዎች ተሟልቶላቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራም እንደሚሰራ ተነግሯል፡፡

የኮሮና ቫይረስ በተከሰተበት ወቅት ጭምር ሀገራቱ ባላቸው የትብብር ስምምነት መሰረት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በጋራ መሰራቱን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውሷል፡፡

ልዑኩ በሚያደርገው የስራ ጉብኝት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይሆን ሀገራቱ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው እና በቀጣይ መሰል የስደተኞች አያያዝ  ችግሮች እንዳይከሰቱ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም እንደሚመክር ተገልጿል፡፡

የልዑክ ቡድኑ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የተውጣጣ መሆኑንም ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡