በቢሾፍቱ ከተማ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ ነው

ሰኔ 12/2013 (ዋልታ) – በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ሰኔ 14 ለሚደረገው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ ነው።

በከተማ አስተዳደሩ የምርጫ ቁሳቁስ ወደተዘጋጁ  የምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።

በአስተዳደሩ በአንድ የምርጫ ክልል 113 የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫው እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡

በከተማዋ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም ብልፅግና፣ አብን እና ኢዜማ ለፌደራል እና ክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መሆናቸው ተጠቁሟል።

በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የአድአ አንድ ምርጫ ክልል ኃላፊ መሰረት አበበ የህዝብ ደምፅ መስጫ ወረቀት፣ የድምፅ መስጫ ሳጥን፣ የሚስጥር ቦታዎች እንዲሁም የኮቪድ-19 መከላከያ ከተሰራጩት ቁሳቁስ መካከል እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በ113 የምርጫ ጣቢያዎች 83 ሺህ 669 መራጮች ድምፅ ለመስጠት የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውንም ሀላፊው ተናግረዋል።

በምርጫው እለት መራጮች አርንጓዴ አሻራቸውን እንዲያሳርፉም ችግኞች መዘጋጀታቸው ታውቋል።

(በትዕግስት ዘላለም)