የምርጫው የእስካሁን ሂደት በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ ነው – የአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን

የአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን

ሰኔ 14/2013 (ዋልታ) – የምርጫው የእስካሁን ሂደት በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ገለጹ።

የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ዛሬ ረፋዱ ላይ በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 21/22 ምርጫ ጣቢያ 4 እና 5 የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በአካል ተገኝቶ ታዝቧል።

የቡድኑ መሪ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፤ “ቡድኑ ከገባበት ቀን ጀምሮ የምርጫ ሂደቱን በተለያየ መልኩ ሲከታተል ነበር” ብለዋል።

የምርጫ ዝግጅቱን በተመለከተ አፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው ሠፋ ያለ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከጸጥታ ተቋማት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከሌሎች አካላት ጋር የምርጫውን ዝግጅት በተመለከተ መወያየታቸውንም አስታውሰዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሺን፣ የጸጥታና የሎጅስቲክስ ችግሮች ቢስተዋሉም የምርጫ አስፈጻሚ አካላት ይህንን ተቋቁመው ምርጫውን ማስፈጸማቸውን ጠቁመዋል።

የምርጫው የእስካሁን ሂደትና የዛሬ ድምጽ አሰጣጥ በመልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የቡድኑ መሪ ገልጸዋል።

ቡድኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ የክልል የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሂደቱን ተዘዋውሮ መመልከቱን ጠቁመው፤ “የእስስካሁኑ ሂደት ጥሩ ደረጃ ላይ ነው” ብለዋል።

መራጩ ህዝብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ በመረዳትና በመተግበር ምርጫው ቅደም ተከተላዊ ሥነ-ሥርዓቱን በተከተለ መልኩ እየተከናዋነ መሆኑን አስረድተዋል።

“መራጩ ከንጋት 12፡00 ጀምሮ ድምጽ መስጠት መጀመሩንም ተረድቻለው” ብለዋል።

በምርጫው ተሳታፊ የሆኑ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ማነጋገራቸውን ገልጸው፤ እስካሁን ቅሬታ ያቀረበ ፓርቲ አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

ከዚህ በኋላም በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች በመዘዋወር የምርጫ ሂደቱን እንደሚታዘብ የአፍሪካኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን መግለፁን ኢዜአ ዘግቧል።