በዳዉሮ ዞን የምርጫው ሂደት በሠላማዊ መንገድ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገለጸ

ሰኔ 14/2013 (ዋልታ) – በዳዉሮ ዞን 2 የምርጫ ክልሎች የምርጫው ሂደት በሠላማዊ መንገድ እየተከናወነ እንደሚገኝ የዳዉሮ ዞን የምርጫ ቦርድ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የዞኑ የምርጫ ቦርድ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር በተላ በየነ እንደገለጹት፣ ከቀናት በፊት በሁለት የምርጫ ክልሎች የምርጫውን ሂደት ለማሳካት የሚያግዙ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ክልሎች በሠላማዊ መንገድ ለማሰራጨት ተችሏል፡፡

በሁለት የምርጫ ክልሎች 186 የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የፖለቲካ ፓርቲ ታዛቢዎች እና አስፈጻሚ ኮሚቴዎች በተገኙበት ከማለዳው 12፡00 ጀምሮ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል፡፡

በዞኑ የሚገኙ መራጮች የምርጫ ሂደቱ እንዲደናቀፍ ከሚፈልጉ አንዳንድ ኃይሎች ታቅበው ድምጽ እየሰጡ ይገኛሉም ብለዋል፡፡

አንዳንድ ግለሰቦች በማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ሂደቱን ለማጠልሸት የሚያናፍሱ እና የአካባቢውን ገጽታ ለማበላሸት መረጃና ማስረጃ አልባ ወሬዎችን በመለየት የህግ በላይነትን የማስከበር ሂደቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በህግ የማስከበሩ ዘመቻም የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የገለጹ ኃላፊው፣ እስካሁን ባለው ሂደት ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡

በዳዉሮ ዞን የምርጫው ሂደት

የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ምንም እንኳን በበላይነት የሚመራ ቢሆንም፣ በየደረጃው ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎችና የፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት በጥምረት እየተሠራ እንደሚገኝ ማረጋገጡን የደሬቴድ ዘግቧል፡፡