የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ስራ ጀመረ

ሰኔ 15/2013 (ዋልታ) – በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተገነባው 5ኛ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከልን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በይፋ ስራ አስጀምረዋል።

ትጋታችን ይቀጥላል እርስበእርስ በመረዳዳት እና በመተሳሰብ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ሲጠናክር ታሪክ እንሰራለን ያሉት ምክትል ከንቲባዋ በትላንትናው እለት ያደረግነው ምርጫ በተግባር ያሳየንበትም ነው ብለዋል።

ዛሬም ሆነ ከዚህ ቀደም የተከፈቱት የምገባ ማዕከላት አቅመ ደካሞችን፣ እናቶች እና አረጋውያንን ከመመገብ ባሻገር መስራት ለሚችሉ ወገኖች የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን ወ/ሮ አዳነች ገልጸዋል።

ዛሬ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስራውን በይፋ የጀመረው ማዕከሉ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን አማካኝነት የተገነባ ሲሆን የኢትዮጵያ ጠለፋ መድህን አክሲዮን ማህበር የ5 ሚሊዮን ብር፣ ሮሃ ሜዲካል ካምፓስ ሔልዝ ፋውንዴሽን 1.5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።