በካናዳ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ106 ሺህ የካናዳ ዶላር በላይ ተሰበሰበ

ሰኔ 18/2013 (ዋልታ) – በካናዳ ማኒቶባ ግዛት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ106ሺህ የካናዳ ዶላር በላይ ተሰብስቧል።

በካናዳ የተቋቋመው ጥምረት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የማኒቶባ ቻፕተር በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በማኒቶባ ግዛት በዊኒፔግ ከተማ እና ብራንደን ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ባዘጋጁት የቨርቹዋል ኮንፈረንስ እና የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም 44 ሺህ 575 የካናዳ ዶላር ነጻ ድጋፍ ተደረጓል፡፡

እንዲሁም 13 ሺህ 550 ነጻ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የተገባ ሲሆን፣ በተጨማሪም 47 ሺህ 900 የካናዳ ዶላር የቦንድ ግዢ በቀጥታ ከአገር ቤት ለመፈጸም ቃል ተገብቷል።

ፕሮግራሙ በተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች ቡራኬ የተጀመረ ሲሆን ባስተላለፉት መልዕክትም ኢትዮጵያዊያን በዚህ ወሳኝ ጊዜ በፅናት አብረው በመቆም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ሙሌት እንዲሳካ ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በካናዳ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ላይ ካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረጉ የሚገኙት ተከታታይ የገቢ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴ የሚያኮራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሯ በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ከሚገኙ የጥምረት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቻፕተሮች ጋር በመተባበር አስካሁን በተካሄዱ 15 መድረኮች በስጦታ ብቻ ከ376 ሺህ የካናዳ ዶላር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አብራርተዋል።

አምባሳደር ናሲሴ በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ያላቸው ፍቅር እና ለጋስነታቸው ታላቅ አርአያ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ካለችበት ውስብስብ ሁኔታና የራሷን ተፈጥሮ ሃብት ተጠቅማ ዜጎቿን ከድህነት ለማላቀቅ የምታደርገውን ጥረት ለማሰናከል ከውስጥና ከውጭ ከተጋረጠባት ጫና አንፃር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ ላይ አርበኛ በመሆን የሚያደርገውን ዘርፈ ብዙ ድጋፎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ በውሃ ሀብት ልማት ዘርፍ የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ እንዲሁም ሰለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተለያዩ ታዋቂ ሚዲያዎች ላይ ቀርባ በመሟገት የምትታወቀው ወጣት መቅደላዊት መሳይ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ያለውን ጠቀሜታና ግድቡ የመልማትና የህልውና ጥያቄ እንዲሁም የዘላቂ ልማት ግቦች ማሳኪያ ቁልፍ መሆኑን ለታዳሚዎቹ ገልፃለች፡፡

የጥምረት ለታላቁ የህዳሴ ግድብ በካናዳ የስራ አስፈጻሚ አባል ዶ/ር ጌቱ ቢፍቱ በበኩላቸው፣ “የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ሙሌት የግድ እንዲከናወን አስፈላጊ የሆነበትን መሰረታዊ ሃሳቦች በማንሳት ገለጻ አቅርበዋል፡፡

እንዲሁም የዳያስፖራ አባላቱ ቦንድ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መግዛት ሰለሚችሉበት ሁኔታ መረጃ ተሰጥቷል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ እናቶች ቀርበው ባስተላለፉት መልዕክት ታላቁ ህዳሴ ግድብን መጨረስ ማለት በመብራት እጦት ለማገዶ ለቀማና ውሃ ፍለጋ ረጂም መንገድ በመጓዝ ዕድሜያቸውን ሙሉ በመኳተን ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ ከአገሪቱ ህዝብ ከግማሽ በላይ ቁጥር ያላቸውን ኢትዮጵያውያን እናቶችን፣ ህፃናትንና ወጣቶችን ከጨለማ የሚያወጣ በመሆኑ፤ በውጭ የሚገኙት የዳያስፖራ አባላት የተሻለ ህይወት እየመሩ ስለሚገኙ የአቅማቸውን ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ በማበርከት እነዚህን እናቶች ሊታደጓቸው እንደሚገባ በማሳሰብ የእናትነት ተማፅኗቸውን አቅርበዋል፡፡

የፕሮግራሙ አዘጋጅ የሆኑት የማኒቶባ የጥምረት ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ቻፕተር አመራሮችና አባላት በፕሮግራሙ ላይ የተለያዩ ስሜት ቀስቃሽ እና ከዓባይ ወንዝ ጋር የተያያዙ ግጥሞች በማቅረብ ከፍተኛ የማነሳሳት ስራ ሰርቷል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ተሳታፊዎችም በነጻ ድጋፍና በቦንድ ግዥ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል መግባታቸውን በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።