በትግራይ ክልል የአሸባሪው ሕወሃት ርዝራዥ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ የሰብዓዊ ድጋፍ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ጥቃት ተፈጸመ

ሰኔ 19/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል የአሸባሪው ሕወሃት ርዝራዥ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ የሰብዓዊ ድጋፍ በሚያደርጉ ሁለት ኢትዮጵያውያን እና አንድ ስፔናዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ጥቃቱ አቢ አዲ በተባለ ስፍራ ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን ሰራተኛ በሆኑ ሰዎች ላይ በአሸባሪው ህወሓት የተፈጸመ ነው።

በዚህም መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝቷል።

መንግስት በተደጋጋሚ ለጋሽ እና እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች የፀጥታ እና የስጋት አካባቢዎች ላይ ለሰራተኞች ደህንነት ሲባል ማንኛውም እንቅስቃሴ በመከላከያና በፀጥታ አካላት ታጅበው ለዜጎች እንዲያደርሱ ሲመክር መቆየቱ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ የተወሰኑ ሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች ከመንግስት እውቅና ዉጭ ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል ይህም የከፋ ችግር እያስከተለ መሆኑ ተገልጿል።

የፖለቲካ ትርፍ ለማግኝት ንፁሃንን የሚቀጥፍ የአሸባሪው ህወሃት የተበታተኑ ሽፍታዎችን ለህግ ለማቅረብ መንግስት ዛሬም ህዝባዊነቱን ጠብቆ ለዜጎች ሰላም እና ለአገሪቱ ሉዐላዊነት እንደሚሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።