ሞ ፋራህ ከ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ውጭ ሆነ

ሰኔ 19/2013 (ዋልታ) – የአራት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ሞ ፋራህ ትላንት ምሽት በማንቸስተር በተደረገው የብሪታንያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ድል ቢቀናውም ዝቅተኛውን የኦሎምፒክ ሰዓት ሚኒማውን ማሟላት ባለመቻሉ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል፡፡
አትሌቱ 10ሺህ ኪሎሜትሩን ለመሮጥ 27ደቂቃ ከ47ሰከንድ የፈጀበት ሲሆን በ19 ሴኮንድ ነው ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ውጭ የሆነው።
የአለም 10ሺህ እና 5ሺህ ሜትር የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳለያ ባለቤቱ ሞ ፋራህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረቱን በማራቶን ውድድሮች ላይ ቢያደርግም ስኬታማ መሆን አልቻለም፡፡
ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ በቀረው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ብሪታንያን በ10ሺህ ሜትር ለመወከል የነበረው ፍላጎት ትላንት ምሽት ሳይሳካ መቅረቱን ተከትሎ ሞ ፋራሀን በጃፓኑ ውድድር አንመለከተውም ሲል ስካይ ኒውስ አስነብቧል፡፡
(በሀብታሙ ገደቤ)