የኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ እና ሱዳን የፋይናንስ ሚኒስትሮች በምስራቅ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ ላይ ተወያዩ


ሰኔ 20/2013 (ዋልታ) –
የኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ እና ሱዳን የፋይናንስ ሚኒስትሮች በምስራቅ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ ላይ በጂቡቲ ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ በንግድ፣ ኢነርጂ እንዲሁም ቀጠናዊ ዲጂታል ኢኮኖሚ መስኮች ቀጠናዊ ትስስርን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማመላከት ያለመ ነው።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሺዴ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአውሮፓ ህብረትና የዓለም ባንክ ኢኒሼቲቩ ስኬት ላበረከቱት ያልቋረጠ ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
አያይዘውም ሱዳን የኢኒሼቲቩ ቋሚ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ በአዎንታዊነት እንደሚመለከቱት አንስተው፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ልማት አጀንዳዎች ከኢንሼቲቩ ፕሮግራም ጋር ለማጣጣም ቅድሚያ በመስጠት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የኢኒሼቲቩ የወቅቱ ሊቀ-መንበር የሆኑት የጅቡቲው ፋይናንስ ሚኒስትር ኤያስ ሙሳ ዳዋሌህ በበኩላቸው ኢኒሼቲቩ በቀጠናው ቅድሚያ ለተሰጣቸው ዘርፎች የሚሆን 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ከሶስት አጋሮች መሰባሰቡን መቻሉን ጠቅሰው፣ በቀጠናው ልማት ትኩረት የተሰጣቸው ዘርፎችን ፋይናንስ ለማድረግ እንደሚውል ገልፀዋል።
በፋይናንስ ሚኒስትሮቹ ምክክር ላይ የአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር እና የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በታዛቢነት መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።