ቦርዱ ቅሬታዎች በተነሱባቸው ጣቢያዎች ጉዳዩ እስኪጣራ ቆጠራ እንዲቆም መወሰኑን ገለጸ

   የምርጫ ቦርድ ኮምዩኒኬሽንስ አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ

ሰኔ 20/2013 (ዋልታ) – የምርጫ ቦርድ ኮምዩኒኬሽንስ አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ቅሬታዎች በተነሱባቸው ጣቢያዎች ጉዳዩ እስኪጣራ ቆጠራ እንዲቆም መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በፓርቲዎች የተነሱ አቤቱታዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በዚህም በደቡብ ክልል በቁጫ የምርጫ ክልል ሲካሄድ የነበረው ቆጠራ በነበረው ተገቢ ያልሆኑ አሰራሮች እና የጸጥታ ችግር እንዲቆም መወሰኑን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪዋ ገልጸዋል።

በምርጫ ክልሉ ሲቀርቡ ከነበሩት ቅሬታዎች ባለፈ የጸጥታም ችግር እንዳለ መረጃ ስለደረሰን ቆጠራው ቆሞ የምርጫ ቁሳቁሶች ባለበት ታሽጎ እንዲቀመጥ መወሰኑን ነው ያስታወቁት፡፡

የኮሙዩኒኬሽን አማካሪዋ አዲስ አበባ ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ የምርጫ ጣቢያዎች ነበሩ የተባለውም ሀሰት መሆኑን ጠቁመው ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ኮድ የተሰጣቸው እና የሚታወቁ ናቸው ብለዋል።