ደቡብ አፍሪካ ጠንከር ያሉ አዳዲስ የኮቪድ-19 መቆጣጠሪያ ገደቦችን ይፋ አደረገች

ሰኔ 21/2013 (ዋልታ) – የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአገራቸው ሊከሰት የሚችለውን ሦስተኛውን ዙር የኮሮና ቫይረስ ማዕበል ጉዳት ለመቆጣጠር ጠንከር ያሉ አዳዲስ ገደቦችን ይፋ አደረጉ።

በዚህም ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የአልኮል ሽያጭን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ እና የሐይማኖት ስብሰባዎች ክልከላ ተጥሎባቸዋል።

በተጨማሪም የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የማታ የሰዓት እላፊ ጊዜን ሲያራዝም በሚቀጥለው ሳምንት ትምህርት ቤቶችም ዝግ ይሆናሉ ተብሏል።

በሕንድ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ‘ዴልታ’ የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራጨ የሚገኝ ሲሆን፣ አገሪቱን በጥር ወር ወደነበረችበት ጥብቅ ክልከላ ከመመለሷ በተጨማሪ ባለፈ ቅዳሜ ብቻ ከ18 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተመዝግቧል።

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እየተተገበሩ ያሉት እርምጃዎች የቫይረሱን የስርጭት ፍጥነት እና መጠን ለመቋቋም በቂ አይደሉም ብለዋል።

“በሁሉም መመዘኛዎች ከቀደሞዎቹ የከፋ በሚመስል አውዳሚ ማዕበል ውስጥ ነን፤ የሦስተኛው ማዕበል ጫና ከቀደሙት ሁለቱ ከፍ ያለ ይመስላል” ሲሉም አክለዋል፡፡

የሕዝብ ጤና ተቋማት አቅማቸውን አሟጠው እየሠሩ በመሆናቸው እና የግል ሆስፒታሎችም ችግር ውስጥ በመገኘታቸው አገሪቱ ከባድ ፈተና እየገጠማት መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ አፍሪካ የክትባት ዘመቻ አዝጋሚ ሆኖ እየተጓዘ ነው። ከ59 ሚሊየን ሕዝቧ ውስጥ እስካሁን የተከተቡት 2.5 ሚሊየን ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ፕሬዝዳንቱ አዲስ የሚመጡ ክትባቶች ፕሮግራሙ እንዲፋጠን ያስችላሉ ሲሉም አመላክተዋል፡፡