የምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ


ሰኔ 22/2013 (ዋልታ) – የምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በጀኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተቀመጠ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የማዕከሉን የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
ኢስት አፍሪካ ስኪል ትራንስፎርሜሽን እና ሪጅናል ኢንተግሬሽን ፕሮጀክት (EASTRIP) በምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ሽግግርና ቀጠናዊ ትስስርን ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የመጀመሪያዉ የአምስት ዓመት የልህቀት ማዕከል ፕሮጀክት ግንባታ የሚተገበርባቸው የቀጠናው አገራት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን የልህቀት ማዕከሉ በነዚህ ቀጠናዊ አገራት በ16 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች እንደሚተገበር ተጠቁሟል፡፡
ከነዚህ ውስጥ ጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን ጨምሮ ሰባቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚተገበሩ መሆናቸው ነው የተነገረው፡፡
ለጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 14 ነጥብ 85 ሚሊየን ዶላር ወጪ በአለም ባንክ የሚሸፈን ነው፡፡
በዕለቱ የከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
(በአመለወርቅ መኳንንት)