የግብርና ግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ወቅቱን ጠብቆ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ


ሰኔ 23/2013 (ዋልታ) –
የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ወቅቱን ጠብቆ ለአርሶ አደሮች እያሰራጨ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡
ለግብርና ምርትና ምርታማነት መጨመር የግብርና ግብዓት እና ወቅቱን የጠበቀ ስርጭት ማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓት አቅርቦት ዳይክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ተስፋ ገልፀዋል፡፡
በ2013/14 ምርት ዘመን 18 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የሚደርስ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ከክልሎች የተሰበሰበ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲወዳደር የ24 በመቶ ጭማሪ ወይም የ3 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ልዩነት ታይቷል፡፡
ይህም አርሶአደሮቻችን የግብዓት አጠቃቀም ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን የሣያል ተብሏል፡፡
በዚህም በተያዘው ምርት ዘመን አስካሁን ድረስ 85 በመቶ የሚሆነው ከጅቡቲ ወደብ ደርሶ ወደ ክልሎች እና በእያንዳንዱ ክልል ለአርሶአደሮች ለሚያሰራጩ የህብርት ስራ ማህበራት በመሰራጨት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የአፈር ማዳበሪያ እንደማንኛውም ግዥ ቀላል የሚባል ባለመሆኑ የዓለም አቀፍ የግዥ ጨረታን በወቅቱ ማውጣትን የሚፈልግ በዓለም ላይ ከሚገኙ አገራት በአለም ገበያ ተወዳድረን የምንገዘው በመሆኑ እና ከትራንሰፖረት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ በመሆኑ መንግስት በሚኒስትር መ/ቤቱ በኩል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ይገኛል፡፡
ለአብነት ያህል በዓለም ገበያ የማዳበሪያ ዋጋ ሲጨምር መንግስት ከ4 ቢሊየን ብር በላይ ለዘርፉ ድጋፍ በማድረግ የዋጋ ጭማሪው ከአርሶ አደሮቻችን አቅም በላይ እንዳይሆን ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል፡፡
1 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚደርስ የኬሚካል አቅርቦት እንዲሁም 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ምርጥ ዘር በማሰራጨት ላይ እንደሚገኝ እና በአገራችን ከሚታረሰው መሬት ውስጥ 43 በመቶ የሚሆነው አሲዳማ እና ከዚህ ውስጥ 28 በመቶ የሚሆነው ደግሞ አሲዳማነቱ ከፍተኛ በመሆኑ በኖራ በማከም እና ጤነኛ በማድረግ ለምርትና ምርታማነት መጨመር ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ይገኛል ነው የተባለው፡፡
በተጨማሪ ካሁን በፊት ከመጋዘን አቅርቦት፣ ከትራንስፖርት እና ከጫኝና አውራጅ ጋር ተያይዞ ይገጥሙ የነበሩ ችግሮች እንዲሁም የመረጃ ቅብብሎሽ ችግርን በመፍታት በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት በየተዋረዱ ቅንጅታዊ አሰራር እየሰራ መሆኑን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡