ረቂቅ በጀቱ የሀገሪቱን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እንደሚያቃልል ተገለጸ

ሰኔ 24/2013 (ዋልታ) – የ2014 ዓ.ም ረቂቅ በጀት የሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችንና ድህነት ቅነሳ ተኮር በመሆኑ የሀገሪቱን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እንደሚያቃልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ፡፡

የምክር ቤቱ 6ኛ አመት የስራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለጉባኤ መርምሮ ካፀደቀ በኋላ በፌደራል መንግስት የ2014 ዓ.ም ረቂቅ በጀት ላይ በዝርዝር ሲወያይ በ17ኛ መደበኛ ስብሰባ አጀንዳዎች ላይ መክሯል፡፡

በዚህም ምክር ቤቱ አባላትም በበጀት ዓመቱ የተስተዋሉ ችግሮች በቀጣይ በጀት ዓመት ሊደገሙ አይገባም ያሏቸውን ጥያቄዎች ለገንዘብ ሚንስቴር አቅርበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከምክር ቤቱ አባላት በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ በዋናነትም ፓርላማው በጀት መድቦ ለተቋማት ቢሰጥም በጀት ብክነትን ግን ማስቆም አለመቻሉን እንደ ችግር ያነሱት አንስተዋል፡፡

የሀገር ውስጥ የበጀት ጉድለት ጋር በተገናኙ ጠንካራ የቁጥጥር አሰራሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በቀጣዩ ዓመት ከ334 ቢሊየን በላይ ብር ከታክስ ለመሰብሰብ የታቀደ ቢሆንም የታክስ ገቢ ስርዓታችን ይህንን እቅድ ለማሳካት ችግር እንዳይሆን ይሰራል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለተፈጥሯዊም ሆኑ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምላሽ መስጠትን ያገናዘበ በጀት መያዙንም አንስተዋል፡፡

ሚኒስትሩ የፕሮጀክቶች መጓተት እና ተቋማት ለቤት ኪራይ የሚያወጧቸው ወጪዎችን ለመቀነስ በጀት መመደቡን ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ የፌደራል መንግስት የ2014 ዓ.ም ረቂቅ በጀት ከኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮችን የሚያቃልል መሆን እንደሚገባው የፓርላማ አባላት አሳስበዋል፡፡

መንግስት ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች በቂ የሆኑ የመፍትሄ አሰራሮች ሊዘረጋ ይገባል ያሉት አባላት፣ ገበያው ከአሻጥር የነፃ እንዲሆንና የንግድ ሥርዓቱ በቁጥጥር እንዲመራ መንግስት ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

ምክር ቤቱ አባላቱ የአቅርቦት ሥርዓቱ ቁጥጥር መላላት ዋጋ ንረት ማስከተሉን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ለኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን በቂ የሆኑ የመፍትሄ አሰራሮች መዘርጋታቸውን ጠቁመው፣ ገበያው ከአሻጥር የነፃ እንዲሆንና የንግድ ሥርዓቱ በቁጥጥር እንዲመራ የሚያስችሉ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም መንግስት የኑሮ ውድነት መናር ለመቀነስ የፊሲካልና ገንዘብ ፖሊሲ ለማሻሻል እና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ተጨባጭ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የፓርላማ አባላት አድንቀዋል፡፡

(በደረሰ አማረ)