የቦንጋ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ነገ ይጀምራል

ሰኔ 25/2013 (ዋልታ) – የቦንጋ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የ2013 ዓ.ም ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል።

ጉባኤው “ጥራት ያለው ትምህርት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ የኮሌጁ ዲን አንተነህ አየለ ገልፀዋል።

ኮሌጁ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እና ማሕበረሰብ አገልግሎት ላይ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱንም አቶ አንተነህ ተናግረዋል።

በመሆኑም ከላይ ከተጠቀሱት ሶስት ዋና ዋና ተልኮዎች አንዱ በሆነው የጥናትና ምርምር ዘርፍ የተከናወኑ የጥናት ሥራዎች ከሰኔ 26 እስከ 27/2013 ዓ.ም ለባለድርሻ አካላት የሚቀርቡበት ጉባኤ በኮሌጁ ተዘጋጅቷል ።

በኮሌጁ መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች የተሰሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ለኮሌጁ ማሕበረሰብ እና ለባለድርሻ አካላት የሚቀርቡ ሲሆን፣ ውይይትም ይደረግባቸዋል ተብሏል።

የጥናትና ምርምር ውጤቶቹ በባለድርሻ አካላት ተግባራዊ በሚደረጉበት ሁኔታ ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲያዝ ይደረጋልም ነው የተባለው።

(በነስረዲን ኑሩ)