የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን መልካም እርምጃ የተለያዩ አገሮች በመደገፍ እንዲያግዙ ተጠየቀ

ሰኔ 25/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን መልካም እርምጃ የተለያዩ አገራት በመደገፍ እገዛ እንዲያደርጉ ተጠየቀ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ደመቀ መኮንን የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅብረሰብ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸው የህወሓት ቡድን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በማድረሱ ምክንያት መንግስት በትግራይ ክልል ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻ መግባቱን አብራርተዋል።

ከዘመቻው መጠናቀቅ በኋላም መልሶ ግንባታና ለወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ሌት ተቀን ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።

የህወሓት አሸባሪ ቡድን የሰብዓዊ ድጋፍ ህዝቡ ጋር እንዳይደርስ መሰናክል ሲፈጥር ቢቆይም መንግስት ተቋቁሞ ህዝብን የመደገፍና የመልሶ ግንባታ ስራ ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በህወሃት ቡድን ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ የኤሌክትሪክ፣ የመጠጥ ውሃ፣ የባንክ አገልግሎት እና ኢንተርኔትን ጨምሮ ሌሎች የመሠረተ ልማቶችን በመጠገን ወደ ስራ ማስገባቱንም ገልጸዋል።

ቡድኑ የተጠገኑትን መልሶ በማፍረስ ህዝብ እንዲቸገር በማድረግ የጥፋት ተግባሩን ሲፈፅም መቆየቱንም አቶ ደመቀ ለዲፕሎማቶቹ ገልጸውላቸዋል።

የሽብር ቡድኑ በህዝብ መሃል በመግባት የሚያደርሰውን ጥፋት ቢቀጥልም መንግስት ለሰብአዊነት ቅድሚያ በመስጠት የተናጠል ተኩስ አቁም በማድርግ ሰራዊቱ ከአካባቢው ለቅቆ መውጣቱን አብራርተዋል።

የመንግስት ውሳኔ የክልሉ ነዋሪዎች በክረምቱ ወራት በእርሻ ሥራቸው ላይ እንዲያተክሩ እና የከፋ ችግር እንዳይከሰት ለማድረግ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን መልካም እርምጃ የሀገራት መንግስታት በቅጡ እንዲገነዘቡ እንፈልጋለን ብለዋል አቶ ደመቀ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ የተከሰተውን ቀውስ ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

መንግስት ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅብረሰቡ እና ከአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ለዘላቂ ሰላምና ልማት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአገራት መንግስታት የኢትዮጵያን በጎ ተግባር በመገንዘብ ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉ አቶ ደመቀ ጠይቀዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ዲፕሎማቲክ ማኅብረሰብ አባላት በተሰጣቸው ማብራሪያ መንግስት የወሰደውን እርምጃና የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ በአግባቡ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ መንግስት በትግራይ ክልል በተግባር ያሳየውን የተኩስ አቁም ዲፕሎማቶቹ አድንቀው፣ ለዘላቂ ሰላም መስራት እንደሚገባም መጠቆማቸውን አምባሳደር ሬድዋን ጠቅሰዋል።

በትግራይ ክልል የተደረገው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት መሆኑን መንግስት መግለጹ ይታወቃል።