በ3ኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርኃግብር እስካሁን ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክሏል- የግብርና ሚኒስቴር

ሰኔ 28/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ በተያዘው ክረምት ከስድስት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን፣ እስካሁን ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ የ3ኛውን ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በአቃቂ ወረዳ ቢልብሎ ተፋሰስ ላይ በዛሬው ዕለት አስጀምሯል፡፡

በዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዲኖራቸው ለማድረግ ሀገራዊ ንቅናቄ መፍጠር እና የእቅዱን ዘላቂነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ተቋማዊ ለማድረግ እንደሚሰራ የግብርና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ አሁንም ሁሉም እንደራሱ በማየት ሊንከባከባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በመርሃግብሩ ባለፉት ሁለት ዙሮች በአከባቢው ላይ የተተከሉ ችግኞች የተጎበኙ ሲሆን፣ ለችግኞች የሚደረገው እንክብካቤ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ በአፈር መሸርሸር ብቻ ከ150 እስከ 200 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር አፈር በጎርፍ የሚታጣ ሲሆን፣ አፈሩን ማጣት ብቻም ሳይሆን የገፀ ምድር ውሃ በቀላሉ እንዲጠፋም ምክኒያት ይሆናል ነው የተባለው፡፡

ተፈጥሮ ሀብቱን ለመጠበቅ ትልቅ መሰረት የሆነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አበረታች ለውጦችን እያመጣ ይገኛል ተብሏል፡፡

በአቃቂ ወረዳ በብልብሎ ተፈሰስ ላይ ባለፉት ሁለት ዙር የተተከሉ ችግኞች ለዚህ ምስክር መሆናቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ የአከባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

(በሚልኪያስ አዱኛ)