ከ58 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ቁሶች ተያዙ

ሰኔ 29/2013 (ዋልታ) – ባሳለፍነው ሳምንት ከሰኔ 18 እስከ 25/2013 ዓ.ም ድረስ ከ58 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

እቃዎቹ ከሀገር ሊወጡ እና ወደሀገር ሊገቡ ሲሉ የተያዙ ሲሆን፣ የገቢ ኮንትሮባንድ 54 ሚሊየን 20ሺህ 270 ብር፣ ወጪ ደግሞ 4 ሚሊየን 824 ሺህ 957 ብር ግምት እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡

ከተያዙት ኮንትሮባንድ ቁሳቁስ መካከል የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ ወርቅ፣ የተለያዩ አልባሳት፣ ጫማ፣ ምግብ ነክ፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ኮስሞቲክስ፣ ሲጋራ፣ ልባሽ ጨርቅ፣ መለዋወጫ፣ የሰው መድኃኒትና ሌሎችም የሚገኙበት ሲሆን፣ 19 ያህል ተሽከርካሪዎች ኮንትሮባንድ ሲያዘዋውሩ ተይዘዋል፡፡

ሁሉም የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የኮንትሮባንድ እቃዎችን በመያዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የተወጡ ሲሆን፣ ጅግጅጋ፣ አቃቂ ቃሊቲ እና ሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከፍተኛውን የኮንትሮባንድ እቃዎች የያዙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው ህብረተሰቡ እንዲሁም የፌደራልና የክልል የጸጥታ አካላት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ምስጋና ቀርቧል፡፡