የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በ2ኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

ሰኔ 29/2013 (ዋልታ) – የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለሁለት ዓመታት በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 104 ተማሪዎችን አስመረቀ።

ተመራቂዎቹ በፌዴራል ስተዲስ፣ በሊደርሺፕ፣ በፒስ ኤንድ ኮንፍሊክት፣ በኮንፍሊክት ስተዲስ፣ በዴቬሎፕመንት ኮሙዩኒኬሽን ኤንድ ሚዲያ እንዲሁም በፐብሊክ ፖሊሲ የትምህርት ዘርፎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።

በምረቃ መርኃግብሩ ላይ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አባገዳዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሰቦች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአዲስ መልክ የተዋቀረውን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ መርቀው መክፈታቸው ይታወሳል።

አካዳሚው በሱሉልታ ከተማ በአርባ ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ ሲሆን፣ አጠቃላይ የግንባታ ወጪው 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሆኑ ይታወቃል።