የኢትዮ – ሩሲያ 11ኛው ወታደራዊ የቴክኒክ ትብብር የጋራ ውይይት እየተካሄደ ነው 

ሰኔ 30/2013 (ዋልታ) – የኢትዮ – ሩሲያ 11ኛው ወታደራዊ የቴክኒክ ትብብር የጋራ ውይይት በአዲስ አበባ መኮንኖች ክበብ እየተካሄደ ነው።

የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ትብብር ማጠናከርን ዓላማ ያደረገው ይህ ውይይት ከዚህ በፊት የተደረገውን 10ኛውን የወታደራዊ ቴክኒክ ፕሮግራም አጀንዳ በማየት እንደሚያጸድቅ ተጠቁሟል፡፡

በአሁኑ በ11ኛው ወታደራዊ የቴክኒክ ትብብር ላይም እየመከረ የሚገኝ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን እና የሩሲያን ወታደራዊ ቴክኖሎጂ፣ ክህሎት እና እውቀት ማሳደግ ላይ ነው ያተኮረው፡፡

በመክፈቻው ስነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የመከላከያ ፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፣ ሁለቱ ሀገራት ከ1898 ጀምሮ በዲፕሎማሲ፣ በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ መስክ ታሪካዊና ጠንካራ ግንኙነት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተው ከመከሩ ወዲህ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በጣም ጥብቅ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የህግ ማስከበር ዘመቻ ስታደርግ ሩሲያ የውስጥ ጉዳያችን እንደሆነ አቋም ይዛ በመንቀሳቀሷ፣ ባደረግነው 6ኛው ምርጫ፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጎን ቆማ ወዳጅነቷን በማሳየቷ ሚኒስትር ደኤታዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዚህን ስብሰባ ውጤትንም የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ እንደሚደረግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በሩሲያ ፌዴሬሽን የወታደራዊ የቴክኒክ ትብብር ምክትል ዳይሬክተር ፑንቹክ አናቶሊ የቆየ ወዳጅነት አለን፤ በወታደራዊ መስክ ብዙ የኢትዮጵያ መከላከያ አባላት በሩሲያ ስልጠና ወስደዋል ያሉ ሲሆን፣ ይህ ስብሰባም የሁለቱን ሀገራት የቆየ ወዳጅነት የሚያሳድግ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

የመከላከያ ኢንዱስትሪ እና ደጀን አቭዬሽንን የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ እየተደረገ ያለውን ስራ በጋራ እንደሚያጎለብቱም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል የመከላከያ ፋይናንስ ዘርፍ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ አየር ሀይል እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በውይይቱ ተሳታፊ ሲሆኑ፣ በሩሲያ በኩሉ ደግሞ፣ በኢትዮጵያ የሩሲያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተሬከሂን ኢቭጌኒ እንዲሁም በሩሲያ መከላከያ ቴክኒካል ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎች አባላት መሳተፋቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።