በመዲናዋ በአንድ ጀምበር ከአንድ ሚሊየን በላይ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው

ሐምሌ 02/2013 (ዋልታ) – የፊታችን እሁድ በመዲናዋ በአንድ ጀምበር ከአንድ ሚሊየን በላይ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ጺዮን ተሾመ “ኑ አዲስ አበባን እናልብስ” በሚል ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር በተለያዩ ስፍራዎች እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዚሁ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር አካል የሆነው በአንድ ጀንበር ከአንድ ሚሊየን በላይ ችግኝ የመትከል መርሐግብር የፊታችን እሁድ ሀምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም በመላው አዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

ለመርሐግብሩ የሚሆን የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ቁፋሮን ጨምሮ ሀገር በቀል እና ለምግብነት እንዲሁም ለአካባቢ ውበት የሚጠቅሙ ችግኞች ከወዲሁ ዝግጁ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በችግኝ ተከላ መርሐግብሩ የፌደራል እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የስፖርት ቤተሰቦች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የጽጥታ አካላት፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ዋና ዳይሬክተሯ መጠቆማቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡