የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ አስጀምረ

ሐምሌ 04/2013 (ዋልታ) – የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) እና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የክልሉ ትምህርት ቢሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃግብር በይፋ አስጀምሯል።

በክልሉ ባለፈው አመት 5.5 ቢሊየን ብር ወጭ በበጎ አድራጎት ተግባር እንደተሸፈነ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ አመትም እስከ 25 ቢሊየን ብር ወጭ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ይሸፈናል ተብሎ ይገመታል።

በኦሮሚያ ክልል በበጎ አድራጎትና የዜግነት አገልግሎት መርኃግብር በዘንድሮ አመት ከ3ሺህ በላይ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በ700 ቀበሌዎች ይገነባሉ ተብሎ ይታሰባል።

ከዚህ በተጨማሪ ከ100 ሺህ በላይ መጽሐፍት ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች በስጦታነት የተሰበሰበ ሲሆን፣ ከ17 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ስጦታ ይሰበሰባል ተብሏል።

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ባዘጋጀው የዘንድሮ የክረምት በጎ አድራጎት 10 ሺህ ለሚደርሱ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ድጋፍ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡ ለ100ሺህ ዜጎች የመሰረተ ትምህርት አገልግሎት ተዘርግቷልም የተባለው።

በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ100ሺህ በላይ ችግኝ በትምህርት ማህበረሰቡ ይተከላል ተብሎም ይጠበቃል።

(በቁምነገር አህመድ)