በወራቤ ከተማ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መርኃግብር ተጀመረ

ሐምሌ 04/2013 (ዋልታ) – በወራቤ ከተማ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መርኃግብር ተጀመረ፡፡

መርኃግብሩን ያስጀመሩት የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያ በርካታ የዲፕሎማሲ ድል ባገኘችበት ማግስት የተጀመረ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንድትከውን የበኩላቸውን የተወጡት ወጣቶች፣ በበጎ ፍቃድ አገልግሎትም በንቃት በመሳተፍ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በከተማዋ የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት መርሃግብር ያስጀመሩት የወራቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ናስር ጀማል በበኩላቸው፣ በከተማው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ ላይ የተሰማሩ ሶስት የወጣት ማህበራት መደራጀታቸውን አውስተው፣ ወጣቶቹ በከተማው ከጽዳት ጅምሮ የደም ልገሳና የአቅመ ደካማ ቤቶችን እድሳት በመከወን ክረምቱን ያሳልፋሉ ብለዋል።

የቤት እድሳቱ የተከናወነላቸው የከተማው ነዋሪዋ ሁልባሌ ኢልቦሮ ክረምት ሲገባ ቤታቸው በማፍሰሱ ይቸገሩ እንደነበር ተናግረው፣ ዕድሳት በመደረጉ ደስተኛ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የወራቤ ከተማ ሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ጽ/ቤት ኃላፊ መህቡባ ሲራጅ 7 ሺህ 14 የሚሆኑ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፍቃድ መርኃግብር ተሳታፊ መሆን እንደጀመሩ ገልጸው፣ እስካሁን የ8.2 ሚሊየን ብር ወጪ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማዳን ተችሏል ብለዋል።

(በእንየው ቢሆነኝ)