አዲስ የሚመሰረተው ፓርላማ ውጤታማ እንዲሆን የሚያግዘው ጽ/ቤት ሊኖረው ይገባል- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ


ሐምሌ 05/2013 (ዋልታ) – አዲስ የሚመሰረተው ፓርላማ ውጤታማ ስራ እንዲሰራ ጠንካራ አደረጃጀት ያለው ጽ/ቤት ሊኖረው ይገባል ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
ሰሞኑን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና የጽ/ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
በምክክር መድረኩ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎና ም/አፈ-ጉባኤ ሽታዬ ምናለን ጨምሮ የም/ቤቱ እና የጽ/ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈውበታል፡፡
አሁን ያለውን የጽ/ቤት አደረጃጀት በመከለስ አማራጭ የአደረጃጀት ጥናት ከፍተኛ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የቀረበ ሲሆን የውጭ ሃገራት ተሞክሮን የዳሰሰ ስለመሆኑ የጥናቱ አቅራቢዎች ገልጸዋል፡፡
እንደ ጥናቱ አቅራቢዎች ለሀገራችን ካለው አስፈላጊነት እንዲሁም አቅምን ባገናዘበ መልኩ የየሀገራቱን ልምድ በመቀመር የተዘጋጀው ይህ አደረጃጀት ም/ቤቱን በማዘመን ውጤታማ ስራ እንዲሰራ ያስችለዋል ተብሏል፡፡
የቀረበው የአደረጃጀት ጥናት የም/ቤቱን ስራዎች በጥልቀት የዳሰሰ መሆኑና አሁን በስራ ላይ ያለውን የጽ/ቤት አደረጃጀት ክፍተቶች ለማቃናት እንደሚያግዝ በቀረበው ጥናት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ከፍተኛ አመራሮች ጠቁመው፤ ጥናቱ ሊፈትሻቸው ይገባል ያሉትን ምክረ-ሃሳብም ሰንዝረዋል፡፡
የአደረጃጀት መዋቅሩ ብቻውን ውጤታማ እንደማያደርግና የሰው ኃይል አስተዳደሩና ፍትሃዊ የድልድል መመሪያ ማዘጋጀት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተብሏል፡፡
ም/ቤቱ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች መደገፍ እንደሚኖርበትና ተተኪ ባለሙያዎችንም ማብቃት እንደሚያስፈልግ በነበረው የምክክር መድረክ ስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል፡፡
ም/ቤቱ የአደረጃጀት የጥናቱን ሂደት በቅርበት ሲከታተል እንደነበር የገለጹት የተከበሩ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የአደረጃጀት ሰነዱ ለአስተያየት ክፍት እንደሆነና የተለያዩ ማሻሻያዎች ተደርገውበት እንደሚዳብር ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም የም/ቤቱ ጽ/ቤት ሰራተኞች በአደረጃጀት ሰነዱ ላይ ተወያይተው ተጨማሪ ግብኣት እንደሚሰበሰብ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡