የመከላከያን ሰራዊትን ታሳቢ በማድረግ ለ10 ቀናት የሚቆይ የችግኝ ተከላ መርኃግብር እንደሚካሄድ ተገለጸ

ሐምሌ 06/2013 (ዋልታ) – የሀገርን ሉአላዊነት ለመጠበቅ መስእዋት የሆነውን የመከላከያ ሰራዊትን ታሳቢ በማድረግ ለ10 ቀናት የሚቆይ የችግኝ ተከላ መርኃግብር እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡
በዛሬው እለት ኢትዮጵያን እናልብስ መርኃግብር የመከላከያ ሰራዊት እና የተቋሙ አመራሮች በየካ ክፍለ ከተማ የችግኝ ተከላ መርኃግብር አከናውነዋል፡፡
የነገይቷን ኢትዮጵያ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ለዕድገቷ ተግዳሮት የሆኑትን በጋራ በመስራት ምላሽ መስጠት እንሚያስፈልግና ለዚህም ከአለም ችግሮች መካከል የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እንደ ሀገር የተያዘውን የአረንጓዴ ልማት መርኃግብር እውን ለማድረግ ሀገር በማዳን የተሰለፈው መከላከያም የበኩሉን እንደሚወጣ ተገልጿል፡፡
በዛሬው እለት የተከወነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብርም የመከላከያ ሰራዊት ክብር ታሳቢ በማድረግ ለተከታታይ 10 ቀናት የሚቆይ 300 ሺህ ገደማ ችግኝ እንደሚተከል ተጠቁሟል፡፡
በመርኃግብሩ ተሳታፊ የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ መከላከያ ሰራዊት ሀገር ሉአላዊነቷ ሳይነካ እንድትቀጥል ያደረገ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከወጠናቸው እቅዶች መካከል የሆነውን አረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ተሳታፊ በመሆን ሀገርን ሉአላዊት አድርጎ ከማስቀጠል ባሻገር በዛሬው እለት ለከወነው የችግኝ ተከላ መርኃግብር ክብር ይገባዋል ብለዋል::
ኢትዮጵያ በደም የተገነባች ሉአላዊነቷን ለማስከበር የማይቦዝኑ ልጆች ያሏት ሀገር እንደመሆኗ በቀጣይም ሀገርን ለማስቀጠል ዜጎች ልማታዊ ሀይል ከሆነው ከመከላከያ ሰራዊት ጎን መቆም ያሻል ተብሏል::
(በሄብሮን ዋልታው)