ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው የህዳሴ ግድብ ድርድር ለስኬት እንዲበቃ ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች


ሐምሌ 06/2013 (ዋልታ) –
ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው ድርድር በስኬት እንዲቋጭ ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ በህብረቱ አማካኝነት የሚደረገውን ድርድር በስኬት ለመቋጨት የማይናወጥ አቋም እንዳላት አስታውቋል፡፡ በህብረቱ አማካኝነት የሚካሄደው የድርድር ሂደት ዋነኛ የመፍትሄ አካል መሆኑንም ጠቁሟል ፡፡
ሂደቱም ሃገራቱ ወደሚፈልጉትና ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ እንዲደርሱ ይረዳልም ነው ያለው፡፡
ከዚህ አንጻርም በህብረቱ መሪነት የሚካሄደው ድርድር በስኬት እንዲቋጭና ተቀባይነት ያለው የጋራ ውጤት ይገኝበት ዘንድ ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗንም አስታውቋል፡፡
ድርድሩ በተለያየ ምክንያትና ፖለቲካዊ መልክ እንዲይዝ ጥረት በሚያደርጉ አካላት ሲጓተት መቆየቱን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ ኢትዮጵያ ግልጽ አቋሟን አስቀምጣ የድርድር ሂደቱ በፍጥነት እንዲቋጭ ጥረት ማድረጓን ገልጿል።
ድርድሩ የቆዩ ችግሮችን መፍታት የሚቻልበት ዕድል እንዳለ የጠቀሰው ሚኒስቴሩ፤ “የሶስትዮሽ ድርድሩ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ በሚያደርግ ስምምነት እንዲቋጭ ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት ትሰራለች” ሲል አረጋግጧል።
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በሚያቀርቡት ሃሳብ መሰረት ኢትዮጵያ ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን አመልክቶ፤ ሱዳንና ግብጽም ሂደቱ ፍሬ እንዲያፈራ በትብብር እንዲሰሩ ጠይቋል።